በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሞሮኮ የመሬት መንቀጥቀጥ ያራደው የአትላስ ተራሮች ጫፍ ቱሪዝም ዕጣ ፈንታ


የሞሮኮ የመሬት መንቀጥቀጥ ያራደው የአትላስ ተራሮች ጫፍ ቱሪዝም ዕጣ ፈንታ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:38 0:00

በሞሮኮ የአትላስ ከፍተኛ ተራሮች ላይ የደረሰውና በሦስት ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለው የመሬት መንቀጥቀጥ፣ በአካባቢው እያደገ በነበረውና ለብዙዎች ዋና የሥራ እና የገቢ ምንጭ በኾነው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይም ጉዳት አድርሷል።

በርካታ ጎብኚዎች ወደ አካባቢው ያቀዱትን ጉዞ በመሰረዛቸው፣ በድህነት የሚኖሩት የማኅበረሰቡ አባላት፣ መኖሪያቸውን መልሰው ለመገንባት በሚያደርጉት ጥረት ከገጠሟቸው በርካታ ፈተናዎች አንዱ ኾኗል።

ከፍተኛው የአትላስ ተራሮች ጫፍ የሚገኝበትን እጅግ የተዋበ ወጣ ገባ ስፍራ እና ነዋሪዎቹን የአማዚያህ እና በርበርስ ተወላጆችን ለማየት፣ ጎብኚዎች በየዓመቱ ከልዩ ልዩ የዓለም አካባቢዎች ይተማሉ።

አብዲሳመድ ኤልግዞል፣ የአካባቢው አስጎብኚ ሲኾን፣ “ይህ ባህላዊ የአኗኗር ዘይቤያችን ነው፤” ይላል። “በተራራዎቹ ላይ ስላለው የሰው መስተንግዶ ታውቃላችኹ። በጣም ሰፊ ነው። ፈገግ እያሉ ወጥተው ሰዎችን ሲቀበሉና በቤታቸው ሲጋብዟቸው፣ ለጎብኚዎች ልዩ ስሜት ይሰጣቸዋል፤” ሲልም የጎብኚዎቹን ደስታ ያስረዳል።

የመሬት መንቀጥቀጡ፥ የኤልግዞልን ደንበኞች የሚያስደስቱ በተራራዎቹ ላይ ያሉትን አብዛኞቹን መንደሮች አውድሟቸዋል። እርሱ ይኖርበት የነበረውና ከፍተኛውን የአትላስ ተራራ ለመጎብኘት መነሻ የነበረው የተወሰነው የአሚዝሚዝ ከተማ ክፍልም ፈራርሷል።

በመሬት መንቀጥቀጡ ወደፈራረሰው ቤታቸው ለመመለስ የፈሩት ኤልግዞል እና ጎረቤቶቹ፣ አሁን ውጪ ተኝተው ያድራሉ። በድህነት ውስጥ ለኖረውና እምብዛም ላላደገው አካባቢ፣ ቱሪዝም ያልተጠበቀ መልካም ዕድላቸው ነበር።

የመሬት መንቀጥቀጡ ግን ያን እንደቀየረው፣ ማሮክ የተሰኘው የጎብኚዎች ማረፊያ ሆቴል ባለቤት ብሩኖ ዱቦይስ ይገልጻል።

“የመሬት መንቀጥቀጡ ያደረሰው ጉዳት እጅግ ሰፊ ነው፤” የሚለው ዱቦይስ፣ “ዛሬም ኾነ ከዚኽ በኋላ ለሚኖር ያልታወቀ ጊዜ ማንም ሰው ወደዚኽ አይመጣም። ማንም ሰው!” ሲል ፍርሐቱን ያጋራል።

ፈረንሳዊው የሆቴል ባለቤት ዱቦይስ፣ የመጀመሪያውን ሆቴል በአሚዝሚዝ የከፈተው እ.አ.አ በ2005 ነበር። የመሬት መንቀጥቀጡ ሆቴሉንና ሠራተኞቹን አልነካቸውም። ነባር ደንበኞቹም፣ በምን ሊረዱት እንደሚችሉ ይጠይቁታል።

በአስጎብኚነት የሚተዳደረው ኤልግዞል የወደፊት ዕጣ ፈንታ ግን ገና አልታወቀም። በርግጥ ለአሁኑ፣ አንድ ዓላማ አለው። የመሬት መንቀጥቀጡ ቤት አልባ ለአደረጋቸው ሰዎች፣ መጠለያ ጣቢያን በማዘጋጀት ረድቷል።

ለመርዳት የተቻለውን ሁሉ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጸው አስጎብኚው፣ መጻዒው ጊዜ ግን እንቆቅልሽ እንደኾነበት አመልክቷል። “ምን እንደሚኾን አላውቅም፤ ስለ እርሱ ማሰብም አልፈልግም፤” ይላል፡፡

ኤልግዞል፣ ቤተሰቦቹ ከመሬት መንቀጥቀጡ በመትረፋቸው እጅግ ደስተኛ ነው። ከሁሉም ነገር በላይ ዋናው፣ “እነርሱ በሕይወት መቆየታቸው ነው፤” ሲል ደስታውን አጋርቷል፡፡

XS
SM
MD
LG