ግጭት በበረታበት በዐማራ ክልል፣ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው ጎንደር፣ ትናንት እሁድ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እንደነበር የአሶስዬትድ ፕረስ ዜና ወኪል ነዋሪዎችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የቱሪስት እና የንግድ ማዕከል በሆነችው ጎንደር ከተማ፣ የመንግሥት ሠራዊት ክፍሎች ከፋኖ ሚሊሺያዎች ጋር “በጣም ከባድ ውጊያ” አድርገዋል ሲሉ አንድ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን ያልገለጹ ነዋሪ ለአሶስዬትድ ፕረስ በስልክ ተናግረዋል።
ዛሬ ሰኞ በጎንደር በአብዛኛው ጽጥታ ሰፍኖ መዋሉንና፣ የመንግሥት ሠራዊት ከተማዋን መልሶ መቆጣጠሩን፣ ነገር ግን አልፎ አልፎ ተኩስ እንደሚሰማ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ሱቆች ተዘግተው መዋላቸውን እና መንገዶች ላይ ሰዎች እንደማይታዩ ነዋሪዎች ጭምረው ገልጸዋል።
ባህር ዳርን እና ላሊበላን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ውጊያ አለመስተዋሉን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በበርካታ ቦታዎች የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር መፍረሱን”
መንግሥት የክልሉን ኃይሎች መሣሪያ እንዲያስረክቡ ጥረት ማድረጉን ተከትሎ ባለፈው ሐምሌ በክልሉ በጀመረው ግጭት፣ የፋኖ ኃይሎች በርካታ ከተሞችን ተቆጣጠረው የነበረ ሲሆን፣ ከበርካታ ቀናት በኋላ የመንግሥት ኃይሎች መልሰው ከተሞቹን ተቆጣጥረዋል። በአጸፋው መንግሥት የአስቸኳይ ግዜ ዐዋጅ በክልሉ ላይ በመጣል፣ የኢንተርኔት አገልግሎትን ዘግቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በግጭቱ 180 ሰዎች መሞታቸውን ባለፈው ወር አስታውቆ፣ የዐማራ ተወላጆች በየቦታው በብዛት መያዛቸው እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር።
የአካባቢ ባለሥልጣናት የግድያ ኢላማ በመሆናቸው፣ “በበርካታ ቦታዎች የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር መፍረሱን” በመንግሥት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ወር ማስታወቁን የአሶስዬትድ ፐረስ ዘገባ አስታውሷል።
መድረክ / ፎረም