በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን በተከሰተ የጤና ቀውስ በመቶ የሚቆጠሩ ሕጻናት በመሞት ላይ ናቸው


በሱዳን በተከሰተ የጤና ቀውስ በመቶ የሚቆጠሩ ሕጻናት በመሞት ላይ ናቸው
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:42 0:00

በኩፍኝ፣ ተቅማጥ፣ የተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት እና በሌሎችም መከላከል በሚቻሉ ሕመሞች ሳቢያ፣ ግጭት ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባፈናቀለባት ሱዳን፣ በየወሩ አንድ መቶ የሚሆኑ ሕጻናት ይሞታሉ ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ካለፈው ግንቦት እስከያዝነው መስከረም ወር ድረስ ባለው ግዜ ውስጥ፣ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 1 ሺሕ 200 ሕጻናት በኩፍኝ ወረርሽኝ እና በተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ሕጻናቶቹ ‘ነጭ አባይ’ ተብሎ በሚጠራው ግዛት ባለ የተፈናቃዮች መጠለያ የነበሩ ናቸው ተብሏል።

እንደ ቪኦኤው አክማልን ዳዊ ዘገባ ከሆነ፣ በተቀሩትም የሀገሪቱ ክፍሎች የኮሌራ፣ ደንጌ፣ እና ወባ በሽታዎች በመከሰት ላይ ሲሆኑ፣ በወረርሽኝ ደረጃ እንዳይከሰቱ ስጋት አለ።

“ዕድሜያቸው ከ 5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት በችግሩ ዋና ተጠቂዎች ናቸው። እነርሱም ከታማሚዎቹ 70 በመቶው እና ከሟቾቹም 76 በመቶውን ይይዛሉ፣” ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ዛሬ አስታውቋል።

የጤና ድርጅቱ ማስጠንቀቂያ የመጣው፣ በገንዘብ እና በአቅርቦት ዕጥረት ምክንያት፣ የሀገሪቱ የጤና ዘርፍ ሊንኮታኮት ጫፍ ላይ በደረሰበት ወቅት ነው።

ካለፈው ሚያዚያ ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለው ግጭት፣ በሀገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ ችግር አባብሶታል። የጤና ሚኒስቴሩ፣ ግጭቱ ከጀመረ አንስቶ 1 ሺሕ 500 ሲቪሎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ቢያሳውቅም፣ የዕርዳታ ድርጅቶች ቁጥሩ ከተጠቀሰውም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል በመናገር ላይ ናቸው።

“ከ7.4 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ንጹህ የመጠጥ ውሃ አያገኙም፣ ቢያንስ 7 መቶ ሺሕ የሚሆኑት ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት አደጋ ገጥሟቸዋል” ሲሉ የተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ተናግረዋል።

18 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሱዳናውያን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ 2.57 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንዲደረግ ተመድ ባለፈው ግንቦት ጥሪ አድርጎ ነበር። እስካሁን የተገኘው 778 ሚሊዮኑ ብቻ ነው። ዓለም ሕጻናቱን ከሞት እንዲታደግ ተመድ ጥሪ አድርጓል።

XS
SM
MD
LG