ፕሬዝደንት ባይደን፤ ልጃቸው ሃንተር ባይደን በውጪ ሀገራት ካለው የንግድ ሽርክና ተጠቃሚ ናቸው በሚል ምርመራ እንዲደረግባቸው ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን የአሜሪካው የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ከቪን ማካርቲ ዛሬ አስታውቀዋል።
በባይደን ላይ የቀረበው ክስ “የሙስና ባህል እንዳለ አመላካች ነው” ሲሉ ማካርቲ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።
“ፕሬዝደንት ባይደን የቤተሰባቸውን የውጪ ንግድ ሽርክና በተመለከተ የአሜሪካን ሕዝብ ዋሽተዋል። በርካታ የስልክ ውይይቶች፣ ግንኙነቶች፣ የእራት ግብዣዎች መደረጋቸውን እንዲሁም ተሽከርካሪዎች እና በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወደ ልጃቸው እና የንግድ ሸሪኮቻቸው መላኩን የዐይን ምሥክሮች ቃላቸውን ሰጥተዋል” ብለዋል ማካርቲ።
“20 ሚሊዮን ዶላር ወደ ባይደን የቤተሰብ ዓባላት እንደተላከ የባንክ አካውንት መዝገቦች እንደሚያሳዩ እናውቃለን” ሲሉ አክለዋል ማካርቲ።
ማካርቲ በተጨማሪም፤ የንግድ ግንኙነቱን ለማሳለጥ ባይደን ኦፊሴላዊ ቢሯቸውን ተጠቅመዋል፣ አስተዳደራቸውም ልዩ እገዛ አድርጓል ብለዋል።
የም/ ቤቱ በርካታ ኮሚቴዎች ለውንጀላው ማስረጃ ገና እንዳላቀረቡ የቪኦኤዋ ካትሪን ጂፕሰን ዘገባ አመልክቷል።
በሴኔቱ አብላጫ ቁጥር ያለው የዲሞክራቲክ ፓርቲው መሪ ቸክ ሹመር ምርመራውን “አስቂኝ” ሲሉ አጣጥለውታል።
///
መድረክ / ፎረም