የሕዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት መጠናቀቁን ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ ዛሬ በፌስ ቡክ አስታውቀዋል።
“በውስጥ ፈተና፣ በውጭ ጫና ነበረብን። ከፈጣሪ ጋር የመጣውን ሁሉ ተቋቁመን ለዚህ ደርሰናል” ሲሉ ጽፈዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ኢትዮጵያን ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር ውጥረት ውስጥ የከተተው የሕዳሴ ግድብ ከተጀመረ 12 ዓመታት ተቆጠረዋል። ግብጽ የውሃ ድርሻዋን እንደሚቀንስ በመግልጽ ግንባታውን ስትቃወም እና በግንባታው እና በውሃ አጠቃቀሙ ላይ አሳሪ ስምምነት እንዲኖር ስትጠይቅ ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነትን እንደማትቀበል ስታሳውቅ ቆይታለች፡፡
አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ባለመሆኑ፣ ግድቡ አስፈላጊ እንደሆነ ኢትዮጵያ ትገልጻለች፡፡
ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን፣ ከሁለት ዓመታት በላይ ተቋርጦ የነበረውንና በግድቡ ላይ የሚያደርጉትን ድርድር ከሁለት ሣምንት በፊት ካይሮ ላይ እንደገና ቀጥለው ነበር።
ድርድሩ የቀጠለው፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እና የግብጹ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደል ፋታህ አል ሲሲ፣ በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለውን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ፣ በአራት ወራት ውስጥ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ባለፈው ሐምሌ ማስታወቃቸውን ተከትሎ ነው።
መድረክ / ፎረም