በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅር ዕንቅፋት እንደገጠመው ፕሬዚዳንቱ አስታወቁ


የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅር ዕንቅፋት እንደገጠመው ፕሬዚዳንቱ አስታወቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:45 0:00

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ መዋቅሩን ወደ ኹሉም ዞኖች እና ወረዳዎች እንዳይዘረጋ በተደራጀ ኹኔታ የሚያደናቅፈው አካል መኖሩን፣ ፕሬዚዳንቱ ጌታቸው ረዳ ገለጹ። ለክልሉ ብዙኀን መገናኛ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል ያልኾኑ ወረዳዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ የተቀረጸውን ዐዲስ ማኅተም ለመጠቀም ፈቃደኛ ባለመኾናቸው፣ የመዋቅር ዝርጋታውን እያደናቀፉ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በዚኽም ተጎጂው ሕዝቡ በመኾኑ፣ በምርጫ የተቋቋመ መንግሥት አስተዳደሩን እስኪረከብ ድረስ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥራ ማጠናቀቅ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል፡፡ በጀት መድበው የመዋቅር ዝርጋታውን በተደራጀ መልኩ ያደናቅፋሉ ያሏቸውን ግለሰቦች ማንነት በስም ባይጠቅሱም፣ ጉዳዩ በፓርቲው ግምገማ እንደሚታይ አመልክተዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ፓርቲንና መንግሥትን በመለየት የሚከተለውን ዐዲስ አሠራር፣ በፀረ ህወሓት እንቅስቃሴ የፈረጁ የፓርቲው አመራሮች እንዳሉም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

በክልሉ፣ መንግሥት የማያውቃቸው እስር ቤቶች እንዳሉ በመግለጫው የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በተለይ ኤርትራውያንና የክልሉ ሀብታም ተወላጆች በእስር ቤቶቹ እየታገቱ የማስለቀቂያ ገንዘብ እንደሚጠየቅባቸው ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ኹኔታው፣ እንኳን ለሕዝቡ በእጀባ ለሚሔዱት ባለሥልጣናትም፣ ዋስትና የሚሰጥበት እንዳልኾነ ተናግረዋል።

የክልሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከነገ ጀምሮ የጠሩት ሰላማዊ ሰልፍ መብት እንደኾነ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ፈንጂዎችን በከፍተኛ ደረጃ ከማሰባሰብ አንሥቶ ክልሉን ወደ ሁከት ለማስገባት ያቀዱ ኀይሎች በመኖራቸው፣ ቦታውንና ጊዜውን እንዲቀይር ከአመራሮቹ ጋራ እየተነጋገሩ እንደኾነ አመልክተዋል፡፡ የኹሉም ችግሮች ምንጭ ፖለቲካዊ ቢኾንም፣ የጸጥታ ችግሩን ለመፍታት፣ ከሥራ ውጭ የነበሩ የጸጥታ አካላትን በመመለስ እና ሕዝቡን በማስተባበር ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሠረት የተፈናቃዮች ምለሳ መጓተቱ፣ በተመዘበረው የርዳታ እህል በሕግ እንዲጠየቁ ስለተደረጉ ተጠርጣሪዎች፣ ከጎረቤት ክልል ጋራ ዳግመኛ ወደ ጦርነት ላለመግባት ከፌዴራሉ መንግሥት ጋራ ስለሚከናወኑ ተግባራት፣ አቶ ጌታቸው በመግለጫቸው የዳሰሷቸው ሌሎች ነጥቦች ናቸው፡፡

(ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ)

XS
SM
MD
LG