- የቫግነር አዛዥ ስም ተሳፋሪዎች ዝርዝር ውስጥ አለ ተብሏል
ሩሲያ ውስጥ ከዋና ከተማዋ ከሞስኮ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ በመብረር ላይ የነበረ ጀት ተከስክሶ አስር ተሳፋሪዎች መሞታቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ፡፡ የሩስያው የቅጥር ተዋጊዎች ኩባኒያ የቫግነር አዛዡ ዪቭጊኒ ፕሪጎዢን በአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች ስም ዝርዝር ውስጥ እንዳሉበት ባለስልጣናቱ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በረራው ላይ ተሳፍረው ይሁን አይሁን ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም፡፡
ያልተረጋገጡ ዘገባዎች እንዳሉት አውሮፕላኑ የግል ወታደራዊ ኩባኒያው የቫግነር መሥራች የሆኑት የዪቭጊኒ ፕሪጎዥን ንብረት ነው፡፡ የሩስያው የሲቪል አቪዬሽን ተቆጣጣሪ ተቋም “ሮሳቪያትሲያ” የፕሪጎዢን ስም በተከሰከሰው ጀት የተሳፋሪዎች ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቧል፡፡ ይሁን እንጂ ተሳፍረው ይሁን አይሁን ለጊዜው አልታወቀም፡፡
አውሮፕላኑ ውስጥ ሦስት አብራሪዎች እና ሰባት መንገደኞች እንደነበሩ የሩስያ መንግሥት የዜና አገልግሎት “ታስ” የአጣዳፊ ጉዳዮች ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ከሞስኮ በስተሰሜን ከአንድ መቶ ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ በሚገኘው ትቬር የተባለው ክፍለ ግዛት የደረሰውን አደጋ እየመረመሩ መሆናቸውን የሩስያ ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡
ፕሪጎዢን የግል ወታደራዊ ኩባኒያቸው የቫግነር ተዋጊዎች ዩክሬን ውስጥ ከመደበኛው የሩስያ የጦር ሓይል ጎን ተሰልፈው መዋጋታቸው ሲታወስ ባለፈው ሰኔ ወር ደግሞ በሩስያ ወታደራዊ አመራር ላይ የሞከሩት የትጥቅ አመጽ በአጭሩ እንደጨነገፈ ይታወሳል፡፡
የክሬምሊን ቤተ መንግሥት ዪቭጌኒ ፕሪጎዢን በግዞት ወደቤላሩስ መሄድ ተዋጊዎቻቸውም እዚያው አዛዣቸውን ተከትለው መሄድ፡ መደበኛውን የጦር ሠራዊት መቀላቀል አለዚያ በጡረታ መገለል እንደሚኖርባቸው አስታውቆ ነበር፡፡
መድረክ / ፎረም