በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባዙም በዶክተራቸው ተጎበኙ


ሞሃመድ ባዙም (ፋይል ፎቶ፡ ሮይተርስ)
ሞሃመድ ባዙም (ፋይል ፎቶ፡ ሮይተርስ)

በእገታ ላይ ያሉት የኒጄር ፕሬዝደንት ሞሃመድ ባዙም በዶክተራቸው እንደተጎብኙ ሲገለጥ፣ የናይጄሪያ የሐይማኖት መሪዎች በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን የተቆጣጠሩትን ወታደሮች አነጋግረዋል።

የእስልምና ሐይማኖት መሪዎቹ ወደ ኒጄር መዲና ኒያሜ ያቀኑት፣ የቀጠናው የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኤኮዋስ) የወቅቱ መሪ በሆኑት የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ቦላ ቲንቡ ይሁንታ መሆኑን ኤኤፍፒ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

በኒጄር ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ለመመለስ በሚል፣ የቀጠናው ጦር በተጠንቀቅ እንዲቆም ኤኮዋስ ውሳኔ አሳልፎ ነበር። ትናንት ቅዳሜ ግን የኤኮዋስ ስብሰባ በታቀደለት መሠረት ሳይካሄድ ቀርቷል ተብሏል። “የቀጠናው ጦር ጣልቃ የሚገባ ከሆነ፣ ባዙምን እንገላለን” ሲል ሁንታው ዝቶ ነበር።

የ 63 ዓመቱ ባዙም ከሶስት ሳምንት በፊት በፕሬዝደንታዊ የጥበቃ ኃይሉ መፈቅለ መንግስት ተካሂዶባቸው፣ ከነቤተሰባቸው በመኖሪያቸው ውስጥ በቁም እስር ላይ ይገኛሉ።

ባዙምን የጎበኙት ሃኪም ለእርሳቸውና ለቤተሰባቸው ምግብ ይዘውም እንደሄዱ ታውቋል። የቀደሞው ፕሬዝደንት እና ቤተሰባቸው በቤት ውስጥ ያለው ምግብ አልቆባቸዋል የሚሉ ዘገባዎች ሰሞኑን ሲወጡ ሰንብተዋል።

የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ሂውማን ራይትስ ዎች በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ባዙምን እንዳነጋገራቸው አስታውቋል። ከነቤተሰባቸው “ኢሰብዓዊ እና ጨካኝ አያያዝ” ውስጥ እንዳሉ ባዙም ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG