በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ደጋፊነት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ያለፍርድ እንደታሰሩ ተገለጸ


ከሚሴ ከተማ /ፎቶ ፋይል
ከሚሴ ከተማ /ፎቶ ፋይል

በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ወይም መንግሥት “ሸኔ” እያለ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን ደጋፊነት እና አባልነት ተጠርጥረው የተያዙ 330 ሰዎች፣ በዐማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን በኾነው በከሚሴ ማረሚያ ቤት፣ ከሁለት ዓመታት በላይ ያለፍርድ ታስረው እንደሚገኙ፣ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የልዩ ዞኑ ነዋሪ የኾኑት አቶ አሕመድ ዑመር፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሔድ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ፣ ሁለት ወንድሞቻቸው በቁጥጥር ሥር ውለው፣ ጉዳያቸው ለፍርድ ቤት ቀርቦ በነፃ እንዲለቀቁ እንደታዘዛላቸው ይገልጻሉ፡፡ ይኹንና፣ የዞኑ ፖሊስ ሊፈታቸው ፈቃደኛ ባለመኾኑ፣ አሁንም በእስር ቤት እንደሚገኙ አውስተዋል።

ለዓመታት ያለፍርድ በእስር ላይ ከሚገኙት እስረኞች መካከል አንዱ፣ የወሎ ዘፈኖችን በማቀንቀን የሚታወቀው ሰዓድ አወል ነው፡፡ “ከ40 ጊዜ በላይ ፍ/ቤት ቀርቦ፣ ክሡን በማስረጃ ውድቅ ማድረግ ቢችልም፣ እስከ አሁን በእስር ላይ ይገኛል፤” ሲሉ፣ ቤተሰቦቹ እና የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

በአኹኑ ጊዜ፣ በከሚሴ እስር ቤት ውስጥ፣ 760 እስረኞች ይገኛሉ፡፡ ከእኒኽም ውስጥ 330ዎቹ፣ “በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ደጋፊነት እና አባልነት ተጠርጥረው የተያዙ ናቸው፤” ሲሉ፣ ነዋሪዎቹ ለቪኦኤ ዘጋቢ ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ፣ የመንግሥት ሓላፊዎችን አስተያየት ለማግኘት ጥረት ቢደረግም፣ የልዩ ዞኑ የፍትሕ፣ የጸጥታ እና የደኅንነት፣ እንዲሁም የኮሙኒኬሽን ቢሮው፣ “የዐማራ ክልል በአሁኑ ወቅት በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ሥር ያለ በመኾኑ” ምላሽ ለመስጠት እንደሚቸግራቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የዐማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት፣ ስለ ጉዳዩ ተጠይቆ፣ “ምላሽ ለመስጠት አመቺ ኹኔታ ውስጥ አለመኾኑን” ገልጾ፣ ወደፊት ጉዳዩን በመከታተል ምላሽ እንደሚሰጥ መግለጹን የሪፖርተራችን ገልሞ ዳዊት ዘገባ አመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG