አዲስ አበባ —
ከባሕር ዳር፣ ከጎንደር እና ከሸዋሮቢት ከተሞች ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች፣ ከሰሞኑ የተኩስ ልውውጥ ጋብታ ያገኙት ከተሞቹ፣ በዛሬው ዕለት፣ አንጻራዊ መረጋጋት እና መጠነኛ የነዋሪዎች እንቅስቃሴም እንደሚታይባቸው ገልጸዋል፡፡
ትላንት ጋብ ያለው የተኩስ ድምፅ፣ ዛሬም በከተሞቹ እንዳልተሰማባቸው የጠቀሱ አስተያየት ሰጪዎች፣ ነዋሪዎች ግን፣ በመሠረታዊ አቅርቦቶች እና ግልጋሎቶች ችግር እና በደኅንነት ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
በተያያዘ፣ የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(ዐብን)፣ በዐማራ ክልል ለተፈጠረው ችግር፣ የፌዴራሉንና የክልሉን መንግሥት፣ “በአመራር ብቃት እና ቁርጠኝነት ማነስ” ቀዳሚ ተጠያቂዎች አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ደግሞ፣ ዛሬ በሰጠው መግለጫ፣ በዐማራ ክልል፣ በግጭቱ ለደረሰው ሰብአዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት፣ የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ እንደጀመረ ገልጾ፣ በግጭቱ የሚሳተፉ አካላት፣ የማኅበሩን እንቅስቃሴ ደኅንነት እንዲጠብቁ ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትም፣ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ ኹሉም የግጭቱ ተሳታፊ አካላት፣ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡
መድረክ / ፎረም