ሕንድ፤ በሚቀጥለው ወር ከምታስተናግደው የቡድን 20 አባል አገራት ጉባኤ በፊት በያዘችው የከተማ ጽዳት፣ በዋና ከተማዋ ኒው ደሊ የሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ የጎዳና ላይ ውሾችን ከወዲሁ እያደነቸ መደበቅ መጀመሯ ተነገረ፡፡
የኒው ደሊ ማዘጋጃ ቤት፣ ውሾቹን ከዘመናዊ ትናንሽ ሆቴሎች እንዲሁም በከተማዋ አስደናቂ የቱሪስት መናኽሪያ ከሆኑት እንደ 17ኛው ክፍለ ዘመን ግዙፍ ሐውልት (ሬድሮ ፎርት) ከመሳሰሉት አካባቢዎች፣ የሚያጠምዱ መረቦችን በመጠቀም ለመያዝ ማቀዱን አስታውቋል፡፡
ባለሥልጣናት ትናንት ሐሙስ የማዘጋጃ ቤቱ ሠራተኞች ውሾቹን እያደኑ በመያዝ እንሰሳት ወደሚጸዱበት ማዕከላት እንዲወስዷቸው ማዘዛቸውንም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
"ከእነዚህ ቦታዎች የሚነሱት የጎዳና ውሾች በሙሉ፣ ፕሮግራሙ እስኪያልቅ ድረስ በእንክብካቤ ተይዘውና ተመግብው መቆየት አለባቸው” ይላል ትዕዛዙ።
ሕንድ ባላፈው ዓመት የቡድን 20 ፕሬዚዳንትነቱን ስፍራ ከተቀበለች ወዲህ፣ 30 ሚሊዮን ነዋሪዎች የሚኖሩባትን ኒው ደሊን በማስዋብ ሥራ መጠመዷ ተመልክቷል፡፡
እ.አ.አ በ2012 በተደረገ ቆጠራ ኒው ደሊ ውስጥ ከ60ሺህ በላይ የጎዳና ውሾች እንደሚገኙ ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
መድረክ / ፎረም