የኒዤር ወታደራዊ ቡድን፣ ከፈረሣይ ጋር የነበራቸውን የወታደራዊ ትብብር ስምምነቶች መሰረዛቸውን አስታወቀዋል፡፡
ስምምነቱ የተሰረዘው ከሥልጣን የተወገዱትን የቀድሞ ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙምን በመልቀቅ ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመልሱ የተቀመጠው ቀነ ገደብ በመቃረብ ላይ እያላና፣ ከመፈንቅለ መንግሥት መሪዎች ጋር ተገናኝቶ ለመነጋገር በምዕራብ አፍሪካውያን የተደረገው ጥረት ከተሰናከለ በኋላ ነው፡፡
ትናንት ሐሙስ ማምሻውን በአገሪቱ ቴሌቪዥን ንግግር ያደረጉት የወታደራዊ ቡድኑ ተወካይ አማዱ አብድራማኔ ከኒዤር የቀድሞ ቅኝ ገዥ ፈረንሣይ ጋር የነበሩ ወታደራዊ ስምምነቶች የመቋረጣቸውን ውሳኔ አስታውቀዋል፡፡
ወታደራዊ ቡድኑ በፈረንሣይ ፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በቶጎ፣ እና የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ህብረት (ኤኮዋስ) ጥረትን በምታስተባብረው በአጎራባችዋ ናይጄሪያ፣ በቀድሞ መንግስት የተሾሙትን አምባሳደሮች ማባረረሩን አስታውቋል፡፡
ኤኮዋስ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን ፕሬዚዳንት ባዙምን እስከ ፊታችን እሑድ ወደ ሥልጣን እንዲመልሷቸው ለመፈንቅል መንግሥት መሪዎቹ የጊዜ ገደብ ሰጥቷቸዋል፡፡
እንደ መጨረሻ አማራጭም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ሊከተል እንደሚችል ኢኮዋስ አስጠንቅቋል፡፡
ወታደራዊ መሪዎቹም በሰጡት ምላሽ “ኃይል በኃይል ይመለሳል” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
መድረክ / ፎረም