በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቻይናው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ድንገት መሰወር


የቻይናው የቀድሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ (ፎቶ ፋይል ኤኤፍፒ)
የቻይናው የቀድሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ (ፎቶ ፋይል ኤኤፍፒ)

የቻይናው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ድንገት ከስልጣን ተወግደው መሠወር በዛች ሀገር ላይ ዓለም ያለውን እምነት የሚቀንስ እና የሀገሪቱንም የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ሊያሽመደምድ ይችላል ሲሉ ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው።

የ57 ዓመቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ከአራት ቀናት በፊት የቬትናም እና ስሪ ላንካ አቻዎቻቸውን አግኝተው ካነጋገሩ በኋላ ደብዛቸው ጠፍቷል።

ቺን ጋንግ፣ ከእርሳቸው ቀደም ብለው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት ዋንግ ዪ መተካታቸውን የቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ አስታውቋል።

የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መጀመሪያ ላይ ቺን ጋንግ በጤና እክል ምክንያት እንደተተኩ አስታውቆ ነበር።

“ሁኔታው ቻይና በአንድ ግለሰብ ላይ፣ ማለትም በመሪው ሺ ጂንፒንግ መልካም ፈቃድ ላይ የተንጠለጠለች ሀገር አድርጓታል፣ የመንግስት ሥርዓቱም አደጋ ላይ ወድቋል” ሲሉ በሲንጋፖር ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ በቻይና ፖለቲካ ጉዳይ ላይ ባለሙያ የሆኑት አልፈርድ ዉ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከቺን ጋንግ ጋር የተገናኙ ጽሁፎችን ከድህረ ገጹ ላይ አንስቶ የነበረ ሲሆን፣ ትናንት ዓርብ የተውሰኑ መረጃዎችን መልሶ ለጥፏል። “በመንግስት መ/ቤቶች በኩል መናበብ እንዳልነበረ ያሳያል” ሲሉ ተንታኞች ተናግረዋል።

የቺን ጋንግ ድንገት ከስልጣን መወገድ በግልጽ ምክንያቱ አለመገለጹ እና ያሉበት አለመታወቅ፣ ዲሞክራሲያዊ ሀገሮች ከቻይና ላይ ያላቸውን የትብብር ሁኔታ በጥርጣሬ እንዲያዩት እና እውነተኛ አጋር የመሆኗን ጉዳይ እንደገና እንዲያጤኑ ያደርጋል ሲሉ ተንታኞቹ ጨምረው ገልጸዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG