በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለማዳበሪያ ጥያቄ በሞፈር እና ቀንበር ሰልፍ የወጡ የሃዲያ ዞን አርሶ አደሮች በእስር እና ድብደባ መጎዳታቸውን ገለጹ


በደቡብ ክልል ሃድያ ዞን ሆሳዕና ከተማ፣ ለማዳበሪያ አቅርቦት ጥያቄ፣ ሞፈር እና ቀንበር ይዘው ሰልፍ የወጡ አርሶ አደሮች እንደታሰሩ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናገሩ።

ሰልፉን ለመበተን፣ የዞኑ ፖሊስ በወሰደው ርምጃ፣ አርሶ አደሮቹ እንደተደበደቡና ወደ ሰማይ በተኮሰው ጥይት በመደናገጥ ወድቀው በመረጋገጣቸው እንደተጎዱ ገልጸዋል።

ከዞኑ አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት፣ ባለሥልጣናቱ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመኾናቸው ልናካትት አልቻልንም።

ይኹንና፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ ጉዳዩን እየተከታተለው እንደኾነ አስታውቆ፣ 11 አርሶ አደሮች ለሦስት ቀናት ታስረው እንደነበርና ማምሻውን እንደተለቀቁ አስታውቋል።

ለደኅንነቴ ሲባል ማንነቴ እንዳይገለጥ ያሉን፣ በሃዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ አርሶ አደር፣ በዞኑ የተከሠተውን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት አስመልክቶ አቤቱታቸውን ለማሰማት፣ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ሰልፍ ስለመውጣታቸው፣ በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

በሆሳዕና ከተማ እና በዞኑ የአንዳንድ ወረዳ ከተሞች፣ “ሞፈር እና ቀንበር ይዘን ሰልፍ ወጣን” ካሉን አርሶ አደሮች መካከል፣ ስማቸውን ያልጠቀሱት ሌላው አርሶ አደር፣ በሰልፉ ከተሳተፉት መሀከል፣ 10 አርሶ አደሮች ስለመታሰራቸው ተናግረዋል።

ሰልፉን ለመበተን፣ የዞኑ ፖሊስ ወስዷል ባሉት የኀይል ርምጃ፣ መደብደባቸውንና ወደ ሰማይ በተኮሰው ጥይት በመደናገጥ ወድቀው በመረጋገጣቸው መጎዳታቸውን ገልጸዋል።

ለአርሶ አደሮች ተብሎ የሚመጣው የአፈር ማዳበሪያ፣ ለነጋዴዎች ተላልፎ እንደሚሰጥና በዚኽም ሳቢያ ዋጋው በመወደዱ፣ በግዢ እንኳን ለማግኘት እንዳልቻሉ በመግለጽ አማረዋል።

የመንግሥት ባለሥልጣናትን ምላሽ ለማካተት፥ ለዞኑ ግብርና መምሪያ ሓላፊ፣ ለፖሊስ መምሪያ ፣ እንዲሁም ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ጽሕፈት ቤት ሓላፊዎች ስልክ ብንደውልላቸውም ስለማያነሡ አስተያየታቸውን ለማካተት አልቻልንም።

ይልቁንስ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ በጋሻው እሸቱ፣ ጉዳዩን እየተከታተለ እንደኾነ ጠቁሟል።

የዞኑ ፖሊስ፣ መሣሪያ ወደ ሰማይ በመተኮስ ሰልፉን ለመበተን በወሰደው ርምጃ፣ ጉዳት መድረሱን ገልጸው በሰልፉ ላይ የተሳተፉ አርሶ አደሮች እንደታሰሩ፣ አቶ በጋሻው እሸቱ ተናግረዋል።

በዞኑ፣ ‘የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ለመክፈል’ በሚል ለረጅም ጊዜ ደመወዛቸው የተቋረጠባቸው የመንግሥት ሠራተኞች ጥያቄ በማቅረባቸው፣ ለወራት ታስረው ከቆዩ በኋላ በነፃ እንደተለቀቁ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG