በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በምዕራብ አፍሪካ በመንፈቅ ዓመቱ በተፈጸሙ ከአንድ ሺሕ በላይ የሽብር ጥቃቶች ከአራት ሺሕ በላይ ሰዎች እንደተገደሉ ተገለጸ


በምዕራብ አፍሪካ፣ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ፣ 1ሺሕ800 የሽብር ጥቃቶች ተፈጽመው፣ 4ሺሕ600 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ሲሉ፣ አንድ የቀጣናው ባለሥልጣን አስታውቀዋል።

ጥቃቶቹ፣ ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ እንዳስከተሉም፣ ባለሥልጣኑ ለተመድ የጸጥታው ም/ቤት አስታውቀዋል።

የ15 ሀገራት ስብስቡ - የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በምኅጻሩ “ECOWAS” ፕሬዚዳንት ኦማር ቱሬይ፣ ለጸጥታው ም/ቤት እንደተናገሩት፤ በቀጣናው ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ለስደት ሲጋለጡ፣ 6ነጥብ2 ሚሊዮን የሚኾኑቱ ደግሞ፣ በሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ኾነዋል።

በአኹኑ ወቅት፣ የምግብ ርዳታ ለሚያሻቸው 30 ሚሊዮን ሰዎች፣ ዓለም አቀፍ ምላሽ ካልተሰጠ፣ ቁጥሩ ወደ 42 ሚሊዮን ሊያሻቅብ እንደሚችል፣ ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል።

የሽብር ጥቃት፣ በትጥቅ የታገዘ ዐመፅ፣ የተደራጀ ወንጀል፣ ሕገ መንግሥታዊ ያልኾነ የመንግሥት ለውጥ፣ ሕገ ወጥ የባሕር ላይ እንቅስቃሴ፣ በተፈጥሮ አካባቢ ላይ የሚታይ ቀውስ፣ እንዲሁም የሐሰት ዜናዎች፣ ለቀጣናው የጸጥታ ቀውስ ምክንያት እንደኾኑ፣ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቡ ፕሬዚዳንት አስረድተዋል።

አያይዘውም፣ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ፣ 1ሺሕ800 የሽብር ጥቃቶች ተፈጽመው፣ 4ሺሕ600 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ሲሉ፣ ቱሬይ ለጸጥታው ም/ቤት አስታውቀዋል።

በዴሞክራሲ በኩል የታየው የኋልዮሽ ጉዞ፣ ከጸጥታ ችግር ጋራ ተዳብሎ፣ በምዕራብ አፍሪካ እና በሣህል ቀጣና፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሠቆቃ ዳርጓል፤ ሲሉ፣ ኦማር ቱሬይ ተናግረዋል።

“በተመድ መደበኛ በጀት የሚደገፍ፣ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ኃይል ይመሥረት፤” የሚለውን የአፍሪካ ኅብረት ጥያቄ፣ ኦማር ቱሬይ በጸጥታው ም/ቤት አስተጋብተዋል።

በቀጣናው የሚገኙ የሠራዊት አዛዦች፣ ሁለት አማራጮችን እንዳቀረቡ የጠቀሱት ቱሬይ፣ እነርሱም፣ አምስት ሺሕ አባላት ያሉትን ጦር በ 2ነጥብ3 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ወጪ መመሥረት፤ አልያም፣ በተፈለገ ጊዜ የሚሰማራና በዓመት 360 ሚሊዮን ዶላር የሚመደብለት ሠራዊት ማደራጀት የሚሉት እንደኾኑ ተናግረዋል።

/የዘገባውን ሙሉ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/

XS
SM
MD
LG