በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሙቀት ወጀብ ክፍላተ ዓለምን እያዳረሰ ነው፤ ሀገራት ተጨባጭ ርምጃ እንዲወስዱ ፖፕ ፍራንሲስ በድጋሚ አሳሰቡ


የሙቀት ወጀብ ክፍላተ ዓለምን እያዳረሰ ነው፤ ሀገራት ተጨባጭ ርምጃ እንዲወስዱ ፖፕ ፍራንሲስ በድጋሚ አሳሰቡ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:41 0:00

የዓለም ሙቀት አይሏል፡፡ ከስፔን እስከ ሊባኖስ እና አሜሪካ ድረስ፣ በዚኽ የበጋ ወቅት፣ የሙቀት መጠኑ ከፍተኛውን ደረጃ አስመዝግቧል፡፡

ከእስከ ዛሬዎቹ ከፍተኛው ኾኖ የተመዘገበው ይኸው የሙቀት መጠን፣ በዚኽ ሳምንት፣ በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎችም እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡

በዓለም፣ የአየር ጠባይ ተከታታይ ተቋማት እና ሳይንቲስቶች፣ ኹኔታውን የዓለም ሙቀት መጨመር ከአስከተለው የአየር ንብረት ለውጥ ጋራ አያይዘውታል፡፡ፖፕ አባ ፍራንሲስ፣ የዓለም መሪዎች፣ የአየር ንብረት ለውጡን እንዲዋጉ አሳስበዋል፡፡

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲንስ፣ በትላንት እሑድ መልዕክታቸው፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ በመላው ዓለም በሚገኙ በርካታ ሕያውን ፍጥረታት ላይ ያደረሰውን ችግር ገልጸው፣ ይህን በአፋጣኝ መዋጋት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ፖፕ አባ ፍራንሲስ በዚኹ መልዕክታቸው፣ “የዓለም ሀገራት፣ የብክለት ልቀት መጠንን ለመገደብ፣ ተጨባጭ ነገር እንዲያደርጉ ያቀረብኹትን አቤቱታ በድጋሚ አሰማለኹ፡፡ እጅግ አጣዳፊ ፈተና በመኾኑ፣ ወደ ጎን የማይተውና ኹሉንም ሰው የሚመለከት ነው፡፡ የጋራ ቤታችችንን እንከላከል፤” ብለዋል፡፡

መኖሪያ ቤት የሌላቸው እና እንዲህ ያለውን የአየር ጠባይ ለረዥም ጊዜ ያልተለማመዱ ሰዎች፣ ለአደጋ የተጋለጡ ሊኾን ይችላሉ፤ ሲሉ፣ ኤቢሲ ቴሌቭዥን ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው የካሊፎርኒያ ከንቲባ ግሬስ ኤሌና ጋርነር ፓልም አስጠንቅቀዋል፡፡

“ሰውነትዎ፣ ከዚኽ ከፍተኛ ሙቀት ጋራ ካልተለማመደ፣ የሰውነትዎ የደም ዝውውር ሊሰናከል ይችላል፡፡ አሁን የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመቀነስ የሚያስችሉ ርምጃዎችን እየወሰድን ስለመኾናችን ካላረጋገጥን፣ ይህ እየተባባሰ መሔዱን እናያለን፤” ብለዋል ከንቲባዋ፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ፣ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ስለ መኾኑ፣ በኤቢሲ ቴሌቭዥን - “በዚኽ ሳምንት” በተሰኘው ፕሮግራም ላይ የተጠየቁት፣ የሪፐብሊካኑ ተወካይ ማይክል መኮል፣ “የአየር ንብረቱ እየተቀየረ ነው፡፡ አካባቢያችሁ ሲደርቅ ታውቁታላችኹ፡፡ ለምሳሌ፡- አፍሪካ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየደረቀ ነው፡፡ ያ ሲኾን ደግሞ ከፍተኛ ረኀብ ይነሣል፤ ሽብርተኝነትም የእነዚያ ክትያ ኾኖ ይነሣል፤” ሲሉ መልሰዋል፡፡

በታመቁ ጋዞች ልቀት የታወቁት ቻይና እና ዩናይትድ ስቴትስ፣ ባለፈው ሳምንት፣ ችግሩን እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ተነጋግረዋል፡፡ ይኹን እንጂ፣ ከመነጋገራቸው የወጣ ምንም እመርታ የለም፡፡

በኤቢሲ ቴሌቭዥን “በዚህ ሳምንት” ፕሮግራም ላይ የቀረቡት የዋሽንግተን ክፍለ ግዛት አገረ ገዢ ጄን ኢንስሊ፣ “ለውጥ ለማምጣት የተጨበጡ ሙከራዎችን ማድረግ ያስፈልጋል፤” ይላሉ፡፡

“ይህ ሊፈታ የሚችል ችግር ነው፡፡ ይኹን እንጂ፣ ከቅሪተ አካላት የሚሠሩ የተፈጥሮ ጋዞችን መጠቀም ማቆም አለብን፡፡ በሰብአዊነት ላይ ለሚደርሰው መጠነ ሰፊ ጥቃት መፍትሔው፣ ይህ ብቻ ነው፤” ብለዋል አገረ ገዥው፡፡

የአየር ጠባይ ትንበያ ባለሞያዎች፣ የሙቀት ወጀቦች፣ ለሳምንታት ካልኾነም ለበርካታ ቀናት፣ በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ተንብየዋል፡፡

XS
SM
MD
LG