በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የርዳታ መጠን መቀነስ በኬንያ የሶማልያ ስደተኞችን ለሥቃይ ዳርጓቸዋል


የርዳታ መጠን መቀነስ በኬንያ የሶማልያ ስደተኞችን ለሥቃይ ዳርጓቸዋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:30 0:00

አብዲቃድር ኦማር፣ በግንቦት ወር ከባለቤቱ እና ሰባት ልጆቹ ጋራ፣ ምግብ እና ደኅንነት ፍለጋ፣ ለ12 ቀናት ተጉዞ ኬንያ እስከሚገባ ድረስ፣ ጽንፈኞች በተቆጣጠሩት በሶማሊያ ከተማ መውጫ አጥቶ ይኖር ነበር።አሁን፣ በዓለም ትልቁ በኾነው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ፣ ከፕላስቲክ እና የዛፍ ቅርንጫፎች በተሠራ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ፣ ከቤተሰቦቹ ጋራ ይኖራል።

የ30 ዓመቱ አብዲቃድር፣ ሊያመርተው በሞከረው የደረቀ በቆሎ አጠገብ ቆሞ፣ ኬንያ ውስጥ ሰላም እንጂ ምግብ ማግኘት እንዳልቻለ ይናገራል።

ሩሲያ፣ ከዩክሬን እህል ወደ ዓለም ገበያ እንዲጫን ለማድረግ የተደረሰውን ስምምነት ማቋረጧን ተከትሎ፣ ዓለም ተጨማሪ የምግብ ዋስትና ዕጦት እያስተናገደ ይገኛል፡፡ በዚኽም ላይ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የጸጥታ ችግርን ሸሽተው የሚሰደዱ ሶማልያውያን፣ የሰብአዊ ርዳታ መጠን እየቀነሰ ሲሔድ፣ ምን ሊከሠት እንደሚችል ትልቅ ምሳሌ ኾነዋል።

በግብርና ሥራ ይተዳደር የነበረው አብዲቃድር፣ አብዛኛውን ምርቱን፣ የተወሰነውን የሶማሊያን ክፍል ለተቆጣጠሩትና ከአልቃዒዳ ጋራ ለአበሩት ጽንፈኞች፣ ለበርካታ ዓመታት በቀረጥ መልክ ለመገበር ይገደድ ነበር። ከዚያ የሚተርፈው ጥቂቱ እህል ደግሞ፣ ባለፉት ዐሥርት ዓመታት፣ በድርቅ በተጠቃው ሀገር ለሚኖሩት ቤተሰቦቹ የሚበቃ አይደለም።

በመጨረሻ አብዲቃድር፣ መኖሪያውን ጥሎ ለመሰደድ የወሰነው፣ በሶማሌ ጦር ጥቃት እየደረሰበት ያለው አል-ሻባብ፣ ታናሽ ወንድሙን ሲገድልበት ነው። እናቱም እንደተገደሉበትና በዚያ ለመቆየት እንዳልቻለ የሚገልጸው አብዲቃድር፣ “ለመጓጓዣ ያለን አማራጭ በጣም ውስን ስለነበር፣ የቀሩንን ዕቃዎች አስተካክለን በተሽከርካሪ ተሳፈርን፤” ይላል ስለ ስደቱ ሲናገር፡፡

አብዱቃዲር እና ቤተሰቡ፣ ጥቃቶቹን የሚሸሹ በርካታ ሶማልያውያን ተቀላቀሉ፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት፣ ኬንያ የሚገኘውን ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከተቀላቀሉ 135ሺሕ ዐዲስ ስደተኞች መካከል፣ የአብዲቃድር ቤተሰቦች ይገኙበታል።

ከሶማሊያ ድንበር በ90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በዚኽ ካምፕ፣ የኬንያ መንግሥት፣ የስደተኞች ምዝገባ እንዲቀጥል በየካቲት ወር ፈቃድ መስጠቱን ተከትሎ፣ ስደተኞች የምግብ እርዳታ እንዲያገኙ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ዳዳብ የመጠለያ ጣቢያ፣ ዐዲስ የገቡ ስደተኞችን ጨምሮ፣ ከ360ሺሕ በላይ የተመዘገቡ እና ያልተመዘገቡ ስደተኞች መኖሪያ ነው። ጣቢያው፣ እ.አ.አ በ1990ዎቹ ሲመሠረት፣ በተወሰነው የካምፑ ክፍል በመደዳ የተገነቡት የቆርቆሮ ቤቶች፣ ቋሚ የመኖሪያ አካባቢ የመኾንን ስሜት ይፈጥራሉ። የምግብ ርዳታ ሥርጭቱ ግን፣ እጅግ አሳሳቢ እየኾነ መጥቷል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከለጋሾች የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ እየቀነሰ በመምጣቱ፣ በቀን ይሰጥ የነበረው ቢያንስ 80 ከመቶ የተመጣጠነ ምግብ፣ ወደ 60 ከመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። የሰብአዊ ርዳታ ተቋማት ሰባት ቢሊዮን ዶላር ቢጠይቁም፣ አብዛኞቹ ለጋሽ ሀገራት፣ ትኩረታቸውን ወደ ዩክሬን በማዞራቸው፣ በግንቦት ወር፥ ለኬንያ፣ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በተካሔደው የለጋሾች ጉባኤ የተገኘው ገንዘብ፣ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ይብሱኑ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም 80 ከመቶ የሚኾነውን የስንዴ አቅርቦት፣ ከዩክሬን ለማግኘት የሚያስችለውን ስምምነት ሩሲያ አቋርጣዋለች።

በዳዳብ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሓላፊ፣ ባለፈው ሳምንት መጠለያውን ሲጎበኙ ባደረጉት ንግግር፣ የኹኔታውን ክብደት አስረድተዋል። “በዋናነት የምናየው ጫና፣ የምግብ ዋስትና ዕጦት ነው፤” ሲሉ የገለጹት ሓላፊው፣ በቀን ሦስት ጊዜ ምግብ ያዘጋጁ የነበሩ ቤተሰቦች፣ አሁን፣ በቀን ሁለት ወይም አንድ ጊዜ ብቻ እንደሚያሰናዱና ይህም በጣም ከባድ ክፍተት እንደኾነ አመልክተዋል፡፡ በፕሮግራሙ የሚሰጣቸው ምግብ፣ ቢበዛ ከ20 ቀን በላይ እንደማያቆያቸው የጠቆሙት ሓላፊው፣ ከጓደኞቻቸው እና ከዘመዶቻቸው የሚበደሩ ወይም የሚለምኑ ሰዎች እንደሚታዩ አልሸሸጉም፡፡

በዳዳብ የሚኖሩ ቤተሰቦች፣ በየወሩ፡- ማሽላ፣ ሩዝ፣ ባቄላ፣ በቆሎ፣ የአትክልት ዘይት እና ትኩስ የአትክልት ምርቶችን መግዛት እንዲችሉ፣ ሦስት የአሜሪካ ዶላር ይሰጣቸዋል። ኾኖም፣ መቀነሱን የቀጠለው የምግብ ርዳታ መጠን፣ የምግብ እጥረት በሽታን እያባባሰ ሊሔድ እንደሚችል፣ የርዳታ ሠራተኞች ስጋት አላቸው።

በዓመቱ የመጀመሪያው አጋማሽ ብቻ፣ ከዳዳብ መጠለያ ሦስት ክፍሎች መሀከል፣ ሃጋዴራ በተሰኘው አንደኛው ክፍል ብቻ፣ 384 በምግብ እጥረት በሽታ የተያዙ ሰዎች ተመዝግበዋል። ይህም፣ ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው 347 ሰዎች የበለጠ እንደኾነ፣ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ኮሚቴ አስታውቋል።

በሃጋዴራ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የያዛቸው ሰዎች የሚታከሙበት ሥፍራ፣ ከዐቅሙ በላይ በሚያለቅሱ ሕፃናት ተሞልቷል። ጤና ጣቢያው፣ 30 ሕመምተኞችን ለማስተናግድ ቢቋቋምም፣ በአሁኑ ወቅት 56 ታካሚዎች አሉት። ከእኒኽ አንዷ፣ የ25 ዓመቷ ዱል አብዲራህማን፣ በምግብ እጥረት ከተጠቃችው ልጇ ጋራ ወደዚኽ ሥፍራ የመጣችው በኅዳር ወር ነበር።

ዱል፣ ከቤተሰቦቿ ጋራ ሶማልያን ሸሽታ የተሰደደችው፣ ልጇ፥ ሀይድሮሰፍለስ የተሰኘ፣ በአንጎል ውስጥ በሚከማች ፈሳሽ ምክንያት የሚመጣ የነርቭ በሽታ ከተጠቃች በኋላ ነው። የልጇ ሕመም ከውልደቷ እንደጀመረ የምታወሳው ዱል፣ ገና የሦስት ቀን እያለች፣ በሚጥል በሽታ እንደምትሠቃይ ትናገራለች። “በቂ ምግብ ለማግኘት ብቸገርም፣ ጡት ማጥባቴን ቀጠልኹ።

ሕመሟ ሲብስባት ግን፣ ወደ ሆስፒታል ለማምጣት ከባድ ውሳኔ ወሰንኹ፤” ትላለች፡፡ ኾኖም፣ እስከ አሁን ኹኔታዋ እንዳልተሻሻለና ይህም በእጅጉ እንደሚያሳዝናት ትገልጻለች፡፡

በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ፣ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው፣ የዓለም የስደተኞች ኮሚቴ የጤና አስተባባሪ ባርባራ ሙቲሞስ እንደሚሉት፣ በከፋ የተመጣጠነ ምግብ ዕጦት የሚሠቃዩ ሕፃናትን ለማከም የሚያገለግለው፣ በኦቾሎኒ የበለጸገ ንጥረ ምግብ ሳይቀር፣ በገንዘብ ድጋፍ ማነስ ምክንያት በመቀነሱ፣ የተራቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። “የሰው ኃይልን ጨምሮ እነዚኽን ጉዳዮች ማስተናገድ የምንችልበት እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን የምናክምበት ዐቅማችን ውሱን ነው፤” የሚሉት አስተባባሪው፣ ባለው አነስተኛ ነገርም ቢኾን ለመሥራት እንደወሰኑ ይገልጻሉ፡፡

እንደ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ኮሚቴ፣ እየጨመረ የሚሔደውን የፍልሰተኛ ቁጥር ለማስተናገድ፣ በዐዲስ የመፍትሔ አማራጮች አስፈላጊውን ክብካቤ ለመስጠት እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከገጠሟቸው ፈተናዎች እንዲያገግሙ ለመርዳት ጥረት እያደረጉ እንዳሉ፣ የጤና አስተባባሪው ባርባራ ሙቲሞስ አስረድተዋል፡፡

ስደተኞቹ፣ የደኅንነት ስጋትም አለባቸው። አል-ሻባብ በዚኽ ወር፣ ከድንበር 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሶማሊያ ጦር ሠፈር ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ነበር። የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል፣ ከሀገሪቱ መውጣቱን በቀጠለበት ኹኔታ፣ የሶማሊያ ኃይሎች ጸጥታን የማስከበር ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ ግፊት እየተደረገባቸው ነው።

የኬንያ መንግሥት በበኩሉ፣ ለወደፊቱ፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች፣ ከአገሪቱ ሕዝብ ጋራ ተቀላቅለው መኖር የሚችሉበትን መንገድ፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋራ እየተወያየበት ነው። የተቋሙ የስደተኞች ኤጀንሲ(UNHCR)፣ በተለይ የለጋሾች የገንዘብ ድጋፍ እየቀነሰ በመጣበት ወቅት፣ ስደተኞቹ፣ ከአገሬው ነዋሪ ጋራ ተደባልቀው እንዲኖሩ ማድረግ፣ ተመራጩ መንገድ እንደኾነ ያሠምርበታል።

XS
SM
MD
LG