በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ስድስት ኤጲስ ቆጶሳትን ሾሙ


በትግራይ የሚገኘው አክሱም ጽዮን ቤ/ክርስቲያን (ፎቶ ፋይል)
በትግራይ የሚገኘው አክሱም ጽዮን ቤ/ክርስቲያን (ፎቶ ፋይል)

የትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፈውን የሰላም ጥሪ እና ማሳሰቢያ ባለመቀበል፣ በዛሬው ዕለት (ሐምሌ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ) ስድስት ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመዋል።

ባለፈው ሳምንት እሑድ ከተመረጡት 10 ዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት፣ የቀሪዎቹ አራት አባቶች ሹመት ደግሞ፣ በቀጣይነት እንደሚፈጸም አስታውቀዋል።

የኤጲስ ቆጶሳቱ ሹመት፥ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና የጣሰ፣ ለመዋቅራዊ አንድነቷ እና ለሀገር አጠቃላይ ሰላም አደጋ እንደኾነ የገለጸው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አስተዳደር ጉባኤ እና የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ እንቅስቃሴው እንዲቆም ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ሙሉጌታ ኣጽብሓ በላከው ዘገባ መሠረት፣ በርዕሰ-አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን በተካሔደው ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት የተሾሙት አምስት በአገር ውስጥ እና አንድ በውጭ አገር የሚያገለግሉ አባቶች እንደኾኑ፣ በክልሉ የተቋቋመው፣ ‘መንበረ ሰላማ ከፍተኛ ቤተ ክህነት፣’ የተባለው ተቋም ጸሐፊ መጋቤ ብርሃናት ተስፋይ ሃደራ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡

ዛሬ በአራቱ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት የተሾሙት አባቶች፣ ቃለ መሐላ ፈጽመው፣ በይፋ ወደ ተመደቡበት የአገልግሎት ቦታ እንደሚሸኙ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሐምሌ 5 እና 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ያካሔደውን አስቸኳይ ስብሰባ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ በጦርነቱ ወቅት ለነበረው የመዋቅራዊ ግንኙነት ጉድለት እና የሰብአዊ ድጋፍ እጥረት፣ በይፋዊ መግለጫ ይቅርታ ቢጠይቅም፣ ለይቅርታው አዎንታዊ ምላሽ አለመሰጠቱ በእጅጉ እንዳሳዘነው አመልክቷል።

ከሹመቱ አስቀድሞ የተደረገው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫም፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር ተቀባይነት የሌለው፣ የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊነት የሚጥስና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚጎዳ እንደኾነ በመጥቀስ እንዲቆም ወስኗል።

የኤጲስ ቆጶሳቱ ምርጫም ይኹን ሹመት፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር ተገቢ እንዳልኾነ ገልጾ፣ ሿሚዎቹ ሊቃነ ጳጳሳት፥ ከሕገ ወጥ ድርጊታቸው ታቅበው ለሰላም ውይይት እንዲዘጋጁ የሚያሳስበውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ፣ በትግራይ የተቋቋመውና ራሱን “መንበረ ሰላማ ከፍተኛ ቤተ ክህነት” ብሎ የሚጠራው ክልላዊ ተቋም ጸሐፊ መጋቤ ብርሃናት ተስፋይ ሃደራ አይቀበሉትም፡፡ “በቤተ ክርስቲያኒቷ ሕግ መሠረት፣ በችግር ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ጳጳሳት፣ ዐዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን ይሾማሉ፤” በማለት አስረድተዋል።

“በአሁኑ ጊዜ ትግራይ፣ ችግር ውስጥ ስለምትገኝና ሕዝቡም ተጨማሪ አባት ስለሚያስፈልገው፣ በቀኖናው መሠረት ሹመናል፤” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

“በአሁኑ ጊዜ ከእነርሱ ተለያይተናል፤ ሕጋዊም ሕገ ወጥም ሊሉን አይችሉም፤” በማለትም የቅዱስ ሲኖዶሱን የሰላም ጥሪ እና ማሳሰቢያ ውድቅ ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በዛሬው ዕለት፣ በአክሱም የተሾሙት አባቶች ስድስት እንደኾኑ የገለጹት መጋቤ ብርሃናት ተስፋይ፣ በቀጣይ፣ ቀሪዎቹ አራት ተመራጭ አባቶችም ይሾማሉ፤ ብለዋል:: የሚሾሙበትን ቀን ግን ግልጽ አላደረጉም፡፡

በጉዳዩ ላይ፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መልስ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አስተዳደር ጉባኤ፣ በተጠናቀቀው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ የትግራይ ክልል የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት እና ሉዓላዊነት የሚፈታተን፣ እንዲሁም ማዕከላዊ የመንበረ ፕትርክና መዋቅሯን የሚንድ ሕገ ወጥ አድራጎት ነው፤ በማለት ድርጊቱን ተቃውሟል፡፡

የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ ሰሞኑን በቤተ ክርስቲያኒቱ ቴሌቪዥን በሰጡት ልዩ መግለጫ፣ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ አስቀድሞ፣ የሰላም ኮሚቴ ተቋቁም የዕርቀ ሰላም ጥረት እንዲደረግ፣ የትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት አራቱም ሊቃነ ጳጳሳት ባሉበት ቀርቦ የነበረውን ሐሳብ እንዳልተቀበሉት በማውሳት፣ ለዛሬው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በመንሥኤነት የቀረቡት የበደል ምክንያቶች ቅቡልነት እንደሌላቸው አብራርተዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG