በአፍጋኒስታን የታሊባን አስተዳደር፣ የሴቶች የውበት ሳሎኖች፣ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንዲዘጉ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ይህን ተከትሎም፣ በካቡል የውበት ሳሎን ሠራተኞች የተቃውሞ ሰልፍ ወጥተዋል። ትዕዛዙ ተግባራዊ ከተደረገ፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ሥራቸውን ያጣሉ።
የአስተዳደሩን እገዳ የተቃወሙ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ያካሔዱትን የተቃውሞ ሰልፍ ለመበተን፣ የታሊባን የጸጥታ ኃይሎች የውኃ ቅንቡላ ሲጠቀሙ፣ ወደ አየርም ተኩሰዋል።
ተቃዋሚዎቹ፣ “ሥራችንን አትውሰዱብን” እና “ዳቦ፣ ሥራ፣ ነፃነት እና ፍትሕ” በማለት የተለያዩ መፈክሮችን አሰምተዋል። በሰልፉ ከተሳተፉ ተቃዋሚዎች መካከል፣ አንዲት ስሟን ያልገለጸች ወጣት፣ “አደባባይ የወጣኹት የትምህርት እና የሥራ መብቴን ለመጠየቅ ነው፤” ብላለች፡፡
ታሊባን፣ የውበት ሳሎኖቹ የሚሰጧቸው አገልግሎቶች “በእስልምና የተከለከሉ ናቸው፤” ቢልም፣ ተመሳሳይ የውበት ሳሎኖች፣ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚበዙባቸው አገሮች፣ ያለገደብ ይሠራባቸዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የመረጡት የሚበዙት የተቃውሞው ሰልፈኞች፣ ታሊባን፣ የውበት ሳሎኖችን ለማገድ ያሳለፈው ውሳኔ፣ ሰዎችን የበለጠ ወደ ድህነት እንደሚገፋ አመልክተዋል፡፡ አያይዘውም፣ “በርግጥ፣ ትዕዛዙ ከየት እንደመጣ ማወቅ እንፈልጋለን። ለምንድን ነው የሴቶቹን መተዳደሪያ የሚወስዱባቸው? ለምንድን ነው ሰዎችን ወደ ድህነት የሚገፉት? ወላጆች ሥራ ከሌላቸው፣ እንደምን ልጆቻቸውን ሊመግቡ ይችላሉ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የውበት ሳሎን እገዳው፣ ታሊባን በአፍጋኒስታን ሴቶች ላይ ካሳለፋቸው ተከታታይ ገደቦች ውስጥ፣ በቅርቡ የተላለፈው ነው። ቀደም ሲል፣ ሴቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ዕድል እና ሥራ እንዳያገኙ፣ እንዲሁም የሕዝብ መገልገያ ሥፍራዎችን እንዳይጠቀሙ እገዳ ጥሏል። በስልታዊ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል፣ የስትራቴጂ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል ከፍተኛ ተባባሪ የኾኑት አኒ ፎርዛይመር እንደሚሉት፣ እገዳው ለሴቶች እጅግ አዛኝ ኹኔታ ነው።
በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ እየደረሰ ያለው ነገር በጣም አስከፊ ነው፤ ብዬ አስባለኹ። ይህ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድርና ለሴቶች ሥራ ፈጣሪነት ይደረጋል የተባለውን ድጋፍ የሚቃረን ነው፤ ሲል የጠራውን ይህን እገዳ፣ ታሊባን እንዲያነሣ ጠይቋል።
በካቡል የሚገኘው የውበት ሳሎን ባለቤት የኾነችው አቴና ሀሺሚ በበኩሏ፣ “መላው ካቡል ችግር ውስጥ ነው፤ ያለው፡፡ የውበት ሳሎኖቹ ከተዘጉ፣ ሴቶች ገቢ የሚያገኙበት ሥራ ሊኖራቸው አይችልም፤” ትላለች።
ከአፍጋኒስታን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ምክር ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በካቡል ብቻ፣ ከሦስት ሺሕ በላይ የሴቶች የውበት ሳሎኖች ሲኖሩ፣ በመላው አገሪቱ ደግሞ፣ ወደ 12ሺሕ የሚደርሱ የመዋቢያ ቤቶች አሉ።