በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደቡብ አፍሪካውያን የማንዴላን ቀን አከበሩ


ደቡብ አፍሪካውያን የማንዴላን ቀን አከበሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:14 0:00

· በአገሪቱ “የማንዴላን መንፈስ ያሳዝናል” የተባለው ሙስና አሳሳቢ ኾኗል

ደቡብ አፍሪካውያን፣ የፀረ ዘር መድልዎ ታጋይ እና የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩትን የኔልሰን ማንዴላን ዓለም አቀፍ ቀን፣ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ፣ በፎቶግራፍ ዐውደ ርእይ አክብረው ውለዋል። ማንዴላ፣ ሕይወታቸው ካለፈ 10ኛ ዓመት በተቆጠረበት በዚኽ ወቅት፣ የማኅበረ ኢኮኖሚ መገለሉ እና ሙስናው፣ አሁንም በአገሪቱ ላይ ተንሰራፍቶ ይገኛል።

“የማንዴላ ዓለም አቀፍ ቀን” የተከበረበት ዕለት፣ የማንዴላ 105ኛ የልደት በዓላቸው ነበር።

የፎቶግራፍ ዐውደ ርእዩ የተካሔደው፣ ማንዴላ ከ27 ዓመታት እስር ከተፈቱ በኋላ፣ እ.አ.አ በ1990 ለመጀመሪያ ጊዜ ንግግር ባደረጉበት የኬፕታውን ከተማ ማዘጋጃ ቤት ነው።

ከማንዴላ ወዲህ ነገሮች ተበላሽተዋል። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ከተካሔደ ከ30 ዓመታት በኋላ፣ በአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ(ANC) የሚመራው መንግሥት፣ ሙስናን ለማስወገድ አልቻለም። ኢኮኖሚው በመንገዳገድ ላይ ሲኾን፣ ሚሊዮኖች በድህነት አረንቋ ውስጥ ይማቅቃሉ።

በሲቪል ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ በርካቶች፣ ችግሩን ለመቅረፍ እየሠሩ ነው። “67 ብርድ ልብስ ለማንዴላ” የተሰኘው ትርፋማ ያልኾነ ድርጅት፣ ዜጎች፥ ሹራብ እና መሰል ለብርድ የሚያገለግሉ ልብሶችን ሠርተው፣ ዐቅም ለሌላቸው እንዲሰጥ በማበረታታት ላይ ነው። የማንዴላን ዓለም አቀፍ ቀን ምክንያት በማድረግም፣ የአንገት ልብሶችን በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲያድል ውሏል።

ፍሎረንስ ሬዲ፣ ከድርጅቱ ተወካይ አንዷ ሲኾኑ፣ በሀገር ውስጥ እየኾነ ባለው ነገር እጅግ ተበሳጭተዋል፤ “በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ እየኾነ ያለውን የሚመረምርና ሙስናውን የሚያጋልጥ ሰው እንሻለን። ሙሰኞቹ መጋለጥ እና ለፍርድ መቅረብ፣ እንዲሁም ገለል መደረግ አለባቸው። ልክ ማንዴላ፣ ሀገሩን እንዳስተዳደሩት አድርጎ የሚሠራ መሪ ማግኘት አለብን፤” ብለዋል።

“ሌድልስ ፎር ላቭ” የተሰኘውና 3ሺሕ500 የሚኾኑ መጠለያ የሌላቸውን ሰዎች የሚመግበው ድርጅትም፣ ቀኑን በማስመልከት ሾርባ ሲያድል ውሏል። ዳኒ ዲልቤርቶ፣ የድርጅቱ መሥራች ሲኾኑ፣ “አገሪቱ ባለችበት ኹኔታ ማንዴላ ያዝናሉ፤” ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

“እየኾነ ባለው ነገር፣ ማንዴላ በጣም የሚያዝኑብን ይመስለኛል። እውነቱን ለመናገር፣ ማንዴላ ለአገራችን ያላቸውን ርእይ እና እርሳቸውን ሳስብ፣ በጣም ወደ ኋላ የቀረን ይመስለኛል፤” ሲሉ ተናግረዋል ዳኒ ዲልቤርቶ።

“ኤስኮም” በተሰኘው የኤሌክትሪክ ኮባንያ ውስጥ በተንሰራፋው ሙስና ምክንያት፣ መብራት ለረጅም ጊዜ በመቆራረጥ ላይ ነው። ይህም የዋጋ ግሽበትን፣ የወለድ መጨመርንና የንግድ ቤቶች መዘጋትን አስከትሏል። የሥራ ዐጡ ምጣኔ፣ 30 በመቶ ደርሷል።

በኬፕታውን የአንግሊካን ሊቀ ጳጳስ ታቦ ማኮግባ፣ በማንዴላ የመጨረሻው ዘመን አካባቢ፣ መንፈሳዊ አማካሪያቸው ነበሩ። ሙስና ላይ ትኩረት እንዲደረግ ይሻሉ።

“ማንዴላ እንዳደረጉት፣ የፀረ ሙስና ቡድን ይኑረን፤ አማሳኞችንም እናጋልጥ። ብሔራዊ የዐቃቤ ሕግ ባለሥልጣኑም ኾነ ሌሎች መሥሪያ ቤቶች፣ እነዚኽን አማሳኞች በቁጥጥር ሥር ያድርጉ፤” በማለት ሐሳባቸውን አካፍለዋል። በቂ ወይም ምንም ግልጋሎቶች በሌሉባቸው የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ያለው ኹኔታ አሳዛኝ ነው።

በደቡብ አፍሪካ፣ በቀጣዩ ዓመት፣ አጠቃላይ ምርጫ ይደረጋል። ተንታኞች እንደሚያመለክቱት፣ ኤኤንሲ አሁንም አብላጫ መቀመጫ ይዞ የመቀጠሉን ነገር፣ በርግጠኛነት መናገር ቢቻልም፣ ደጋፊዎቹን እያጣ መሔዱን ግን ይቀጥላል።

XS
SM
MD
LG