በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለሽብር ወንጀል ተከሣሾች የዋስትና ብይን የተቀጠረው ችሎት በዳኛ ቅያሬ ለሌላ ቀጠሮ ተላለፈ


ለሽብር ወንጀል ተከሣሾች የዋስትና ብይን የተቀጠረው ችሎት በዳኛ ቅያሬ ለሌላ ቀጠሮ ተላለፈ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:38 0:00

ለሽብር ወንጀል ተከሣሾች የዋስትና ብይን የተቀጠረው ችሎት በዳኛ ቅያሬ ለሌላ ቀጠሮ ተላለፈ

በሽብር ወንጀል በተከሠሡ ግለሰቦች የዋስትና ጉዳይ ላይ፣ ዛሬ ሊሰጥ የነበረው ብይን፣ በአንድ ዳኛ ቅያሪ ምክንያት ለሌላ ቀጠሮ ተላለፈ፡፡

በዳኛው መቀየር ምክንያት ውሳኔ አለመሰጠቱን የተቃወሙ ተከሣሾች፣ “በማንነታችን የታሰርን የፖለቲካ እስረኞች ነን፤ በፍትሕ ሥርዐቱ ላይም ጥርጣሬ አለን፤” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፣ “እስረኞቹ እንዲህ እያደረጉ ያሉት፣ በዳኞቹ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ነው፤ የሥነ ልቡና ጦርነት ነው፤” ሲል ተቃውሟል፡፡ የተከሣሽ ጠበቆችም፣ “እስረኞች ብሶታቸውንና ጥርጣሬያቸውን የመግለጽ መብት አላቸው፤” ብለው ተከራክረዋል፡፡

ችሎቱም በተመሳሳይ፣ ተከሣሾቹ ሐሳባቸውን የመግለጽ መብት እንዳላቸው ገልጾ፣ በዳኝነት ሒደቱ ላይ ግን ስጋት ሊኖር እንደማይገባ አስገንዝቧል፡፡አንድ ዳኛ ስለተቀየረበት ምክንያት፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን እንደጠየቁ የተናገሩት ከጠበቆች አንዱ ሰሎሞን ገዛኸኝ፣ “ጉዳዩ፣ የፍርድ ቤቱ አስተዳደራዊ ሥራ ነው፤” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

በተከሣሾች የዋስትና ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ተቀጥሮ የነበረው የዛሬው ችሎት፣ ለቀጣዩ ሐምሌ 12 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ችሎቱ ለዛሬ፣ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም የተቀጠረው፣ በእነዶር. ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ ሥር፣ ከአንድ ወር በፊት፣ በዐቃቤ ሕግ የሽብር ወንጀል ክሥ ከተመሠረተባቸው 51 ግለሰቦች መካከል፣ በእስር ላይ የሚገኙ ተከሣሾችን የዋስትና ጉዳይ በተመለከተ፣ ሰኔ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በነበረው ችሎት ክርክር ከተደረገ በኋላ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡

ይኹንና፣ ጉዳዩን እየተመለከቱ ከሚገኙ ሦስት ዳኞች መካከል አንዱ(የግራ ዳኛው) ተቀይረው በሌላ ዳኛ እንደተተኩ የገለጸው ችሎቱ፣ ዛሬ፣ በዋስትናው ጉዳይ ላይ ብይን መስጠት እንደማይችልና በተለዋጭ ቀጠሮ እንደሚመለከተው አስታውቋል፡፡ በታሳሪዎች የተነሡ የመብት ጉዳዮችን ከአዳመጠ በኋላም፣ ከታሳሪዎች አስተያየት እና ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል፡፡

ከተከሣሾቹ አንዷ የኾነችው የዩቲዩብ ብዙኃን መገናኛ አዘጋጅ እና በፖለቲካ ትንታኔዎቿ የምትታወቀው መስከረም አበራ፣ “ዛሬ የመጣኹት ውሳኔ ለመስማት ነበር፤” ካለች በኋላ፣ በዳኛ መቀየር ምክንያት ውሳኔ አለመሰጠቱን እንደምትቃወም ተናግራለች፡፡ “ከ1983 ዓ.ም በኋላ ያለው መንግሥት፣ በዐማራ ላይ እየፈጸመ ያለውን በደል ስለተናገርን ብቻ የታሰርን የፖለቲካ እስረኞች ነን፤” ስትልም ገልጻለች፡፡

አያይዛም፣ “ድምፃችን መታፈን ስላለበት ነው የታሰርነው፤ ልጆቼን እንዳላሳድግ፣ ከልጆቼ ተለይቼ ለእስር የተዳረግኹት ትግሌን እንዳቆም ተፈልጎ ነው፤ ነገር ግን ይበልጥ እበረታለኹ፤” ያለችው መስከረም፣ “በሁከት፣ በሽብር ወይም በገዳይነት እንኳን ብፈረጅ፣ ለልጆቼ በኩራት ነው የምናገረው፤” ስትልም ተደምጣለች፡፡ በችሎቱ የነበሩት የመስከረም እናት፣ ልጃቸው በምትናገርበት ጊዜ ሲያነቡ ተመልክተናል፡፡

አስተያየቱን የሰጠው ሌላው የዩቲዩብ ብዙኃን መገናኛ አዘጋጅ ጎበዜ ሲሳይም እንዲሁ፣ በዋስትና ጉዳይ ላይ በቀጠሮው ብይኑ አለመሰጠቱን ተችቶ፣ በፍትሕ ሥርዐቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳደረበት አመልክቷል፡፡ ዝርዝር ጉዳዮችን ሊያስረዳ በማንሣት ላይ እያለ፣ ዐቃቤ ሕግ፥ “ከተከሠሡበት ጉዳይ ውጭ አስተያየት እየሰጡ ነው፤ የመብት ጉዳይ ካለ ነው ማቅረብ ያለባቸው፤” በማለት ችሎቱ እንዲያስቆምለት ጠይቋል፡፡

ጠበቆች በበኩላቸው፣ ደንበኞቻችን፥ ብሶታቸውን መናገር መብታቸው እንደኾነ በመጥቀስ ተከራክረዋል፡፡ ችሎቱ በሰጠው ምላሽ፣ “በታሳሪዎቹ ጉዳይ፣ ተከሣሾች፥ የፖለቲካ እስረኞች አልያም ጥፋት የፈጸሙ ስለመኾን አለመኾናቸው ሒደቱ ሲጠናቀቅ በስተመጨረሻ በገለልተኝነት ውሳኔ እንሰጣለን፤ ነገር ግን አሁን ላይ፣ የታሰርነው በዚኽ ምክንያት ነው፤ የሚለውን ማቅረብ አስፈላጊ አይደለም፤” ብሏል፡፡ “ዳኞች የተሠየሙት፣ ብሔርን ወክለው አይደለም፤” ያለው ችሎቱ፣ አሁን ውሳኔ መስጠት በሚችልባቸው “የመብት ጉዳዮች ላይ ብቻ፣ አስተያየት እና ጥያቄ ብታቀርቡ” የሚል ምክርም ለግሷል፡፡

አንዱ ዳኛ ለምን እንደተቀየሩ ለቀረበው ጥያቄ፣ “ዳኛ የመቀየር ጉዳይ በአመራሮች የሚከናወን እንደኾነ” በችሎቱ መልስ ተሰጥቷል፡፡ አመራሮች ዳኞችን እየቀየሩ ከቀጠሉ፣ ውሳኔ ሳይሰጥ ፍርድ ቤት የሚዘጋበት ጊዜ ሊደርስ ይችላል፤ የሚል ስጋቱን ያሰማው ሌላው ተከሣሽ ዳዊት በጋሻው፣ በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዐት ላይ ጥርጣሬ አለን፤ ሲልም አክሏል፡፡ “የፖለቲካ እስረኞች ነን፤” በማለት የመስከረምን አስተያየት በድጋሚ ያነሣው ዳዊት፣ “እዚኽ ሁላችንም፣ ዐማራን አትግደሉ፤ ስላልን የታሰርን የኅሊና እስረኞች ነን እንጂ ሰው ስለገደልን፣ ቤት ስላፈረስን፣ አሊያም ስላፈናቀልን አይደለም፤” ካለ በኋላ፣ “የፍትሕ ሥርዐቱ ላይ ጫና እንደሚኖር እናምናለን፤” ሲልም አክሏል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፣ ተከሣሾቹ እያነሡ ያሉት የሥነ ልቡና ጦርነት ነው፤ በዳኝነቱ ላይ ጭምር ጥርጣሬ አለን፤ በማለት ተጽእኖ ለማሳደር እየሞከሩ ነው፤ በመኾኑም፣ ፍርድ ቤቱ ሊያስጠነቅቃቸው ይገባል፤” ሲል ተከራክሯል፡፡ ጠበቆች በበኩላቸው፣ የዐቃቤ ሕግን መከራከሪያ ተቃውመው ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

“ጥርጣሬያችኹንና ብሶታችኹን ልትገልጹ ትችላላችኹ፤ ሰፊ ጊዜ ሰጥተንም ልናዳምጣችኹ እንችላለን፤” ያለው ችሎቱ በበኩሉ፣ “ዳኞች የምንሠራው ለኅሊናችንና ለሕገ መንግሥቱ ታምነን በመኾኑ፣ በዳኝነቱ ላይ ስጋት ሊገባችኹ አይገባም፤” ብሏል፡፡

በቅያሬ ተመድበው ዛሬ ሥራ የጀመሩት ዳኛም፣ የፍትሕ ሒደቱ በመጓተቱ ደስተኛ እንደማይኾኑ ተናግረው፣ “እርሳቸው ዐዲስ የተመደቡ በመኾናቸው፣ የእስካኹኑን ሒደት አንብበው ለውሳኔ እስኪዘጋጁ፣ ቢያንስ አንድ ሳምንት እንዲታገሡ ተከሣሾችን ጠይቀዋል፡፡

የዳኛ መቀየር ያልጠበቁትና ያልገመቱት እንደኾነ የገለጹት ከተሣሳሽ ጠበቆች አንዱ ሰሎሞን ገዛኸኝ፣ ከችሎቱ በኋላ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን፣ ለምን ቅያሪ እንደተደረገ መጠየቃቸውንና “ጉዳዩ፣ የፍርድ ቤቱ አስተዳደራዊ ሥራ ነው፤” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG