ለአራት ቀናት ቻይናን የጎበኙት የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስትር ጃኔት ዬለን በቆይታቸው የነበሯቸው ውይይቶች “ውጤታማ” እንደነበሩ ተናገሩ፡፡
ጉብኝታቸውን ያጠናቀቁት በሁለቱ ኃያላን አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ መሠረት በያዘበት ሁኔታ መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
ዬለን ቤጂንግ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በሰጡት መግለጫ “ዩናይትድ ስቴትስና ቻይና ጉልህ አለመግባባቶች አሏቸው፡፡” ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ግን “እሳቸው እና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን “ዓለም ለሁለቱም አገሮቻችን እድገት በቂ ናት” ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
ዬለን በቻይናው ቆይታቸው ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር 10 ሰዓታትን የፈጀ ውይይቶች ማድረጋቸው ተመልክቷል፡፡
ከዚህ ውስጥ አምስቱን ያህል ሰዓት የፈጀው ከቻይናው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሂ ላይፍንግ ጋር ትናንት ቅዳሜ ያደረጉት ውይይት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ውይይቶቹ “ ሀቀኛ፣ ገንቢ፣ እና ሁሉን አቀፍ “ ነበሩ ብሏል፡፡
የቻይና መንግሥት መገናኛ ብዙሃንም ውይይቶቹ “ጥልቅ፣ ግልጽና ገቢራዊ” ነበሩ ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡
ከቻይናው አዲሱ የኢኮኖሚ አመራር ቡድን ጋር የተወያዩት ዬለን “በዚህ ጉብኝት የኔ ግብ የነበረው በቤጂንግ አዲስ ከተቋቋመው ከዚህ አዲስ የኢኮኖሚ አመራር ቡድን ጋር ግንኙነት መፍጠርና እና ግንኙነቱንም ጥልቅ ማድረግ ነው” ብለዋል፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “ቻይና እና ዩናይትድ ስቴትስ ትብብርና ቅንጅታቸውን ማጠንከር ይኖባቸዋል፡፡” ብሏል፡፡
ሁለቱ አገሮች “ ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን ለመወጣት እና የጋራ ልማቶችን ለማስፋት እጅ ለእጅ መያያዝ ይኖርባቸዋል” ሲልም መግለጫው አመልክቷል፡፡