በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተፈናቃዮች በሚኖሩባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ወባ እየተስፋፋ ነው


ተፈናቃዮች በሚኖሩባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ወባ እየተስፋፋ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:52 0:00

ተፈናቃዮች በሚኖሩባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ወባ እየተስፋፋ ነው

በኦሮሚያ ክልል፣ ተፈናቃዮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች፣ የወባ በሽታ እንደተስፋፋ ተገለጸ። በተለይ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች፣ የሕክምና ተቋማት በመውደማቸው ችግሩ የጎላ እንደኾነ፣ ተፈናቃዮቹ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ በምዕራብ ኦሮሚያ አራቱ የወለጋ ዞኖች ውስጥ በሚካሔደው ግጭት የተነሣ፣ የሰብአዊ ይዞታው አስከፊ በመኾኑ የወባ በሽታ እንደተስፋፋ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UN OCHA) አስታውቋል።

የዞኑ ጤና ጽሕፈት ቤት በበኩሉ፣ የወባ በሽታ የተስፋፋው፣ በተከማቸ ውኃ እና የጸጥታ ማጣት ምክንያት እንደኾነ ገልጾ፣ የመከላከል ጥረት በመደረግ ላይ እንዳለ ጠቁሟል።

ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ተፈናቅለው፣ በጊዳ አያና ወረዳ፣ በሰው ቤት ጣሪያ ሥር ሸራ ወጥረው ከቤተሰቦቻቸው ጋራ የሚኖሩና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ፣ የወባ በሽታው መስፋፋት፥ ተፈናቅለው በችግር ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ ተባብሶ እንደሚታይ ተናግረዋል።

አክለውም ፤ “አሁን ወደ ጊዳ ሆስፒታል መጥታችኹ ብታዩ፣ ከአልጋ እጥረት የተነሳ ሰዉ እየታከመ ያለው፣ ከሆስፒታሉ ውጪ ነው። በወባ ጽናት የተነሳ፣ ብዙ ሕፃናት እና እናቶች እየሞቱ ነው። ሜዳ ላይ የፈሰሱት ተፈናቃዮች፣ ዝናም ሲዘንምባቸው ነው የሚያድረው። ሸራ እንኳን አጥተው እየተቸገሩ ነው። ችግሩ ለመግለጽ የሚያዳግት ነው።” ብለዋል።

ተፈናቅለው በመጡበት ኪረሙ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች፣ ከግጭት የተነሳ የጤና አገልግሎት ከተቋረጠ፣ ሁለት ዓመት ገደማ እንደሆነው ጠቁመዋል። በባጊን፣ ኪረሙ፣ ፍሌዶሮ፣ አሹ ኩሳዬ እና ዋስት በተባሉ ቀበሌዎች፣ ሲሰጥ የነበረው የጤና አገልግሎት እንደተቋረጠም ገልጸዋል።

“በተለይ ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ፣ ከመድኃኒት እጥረት የተነሳ አገልግሎቱ እየተሰጠ አይደለም። መድኃኒት የሚገባበት መንገድ ተዘጋ። የጤና ባለሞያዎችም መድኃኒት ይዘው እየሔዱ ኅብረተሰቡን ያክሙ ነበር።” ያሉት እኒኹ ተፈናቃይ ፣ የጤና ተቋማት በመውደማቸው በተለይ በዋስት እና ፍሌዶሮ ምንም ተቋም እንደሌለ በጊዳ ሆስፒታል እና ጤና ጣቢያ ግን አገልግሎቱ እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

በዚያው በምሥራቅ ወለጋ ዞን ሳሲጋ ወረዳ በሎ ከተማ እንደሚኖሩ በስልክ የገለጹ አስተያየት ሰጪ፣ የወባ ወረርሽኝ በአካባቢያቸው እንደተስፋፋ ተናግረዋል።

በቅርቡ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል በቀረበ መድኃኒት ትንሽ አገልግሎት ማግኘታቸውን የተናገሩት ተፈናቃይ፤ “እሱንም የጸጥታ ችግር ነው ብለው አቋረጡብን። ቀይ መስቀል ያመጣልን መድኃኒት፣ አነስተኛ ስለኾነ እየተዳረሰ አይደለም። ወላድ ለመውለድ የምትሔድበት መንገድ የለም። ስንጠይቅም፣ መድኃኒት የለም፤ እንባላለን። ሰዉ እያለቀ ነው።" ብለዋል።

በዚኽ ላይ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UN OCHA) በምዕራብ ኦሮሚያ አራቱ የወለጋ ዞኖች ውስጥ፣ ከግጭት የተነሳ፣ የሰብአዊ ይዞታው አስከፊ እየኾነ እንደመጣ፣ በዞኖቹ የወባ በሽታን መስፋፋት በመጥቀስ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።

የማስተባበሪያ ቢሮው በሪፖርቱ፣ በአራቱ የወለጋ ዞኖች ውስጥ፣ የሰብአዊ ኹኔታው እየተባባሰ የመጣው፥ እየጣለ ካለው ዝናም በየቦታው ውኃ በማቋሩ የተነሳ የወባ በሽታ ወረርሽኝ በመስፋፋቱ እና በደካማ የጤና ሥርዐቱ ምክንያት እንደኾነ አብራርቷል።

በዚኽም ምክንያት፣ በምዕራብ፣ በምሥራቅ እና በቄለም ወለጋ ዞኖች ውስጥ፣ ከ272 ሺሕ በላይ ሰዎች እንደተጎዱ ገልጿል።

በሌላ በኩል፣ በምዕራብ፣ በምሥራቅ፣ በቄለም ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ፣ ከ45 በመቶ በላይ የጤና ጣቢያዎች እና 63 በመቶ የጤና ኬላዎች፣ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልኾነ፣ የዞኖቹን ባለሥልጣናት በአስረጅነት ይጠቅሳል። ቢሮው ግን፣ ይህን አኃዝ ማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልጿል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ጤና ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ሰሎሞን ጫላ፣ በዚኽ ዓመት፣ በዞኑ የወባ ሥርጭት እንደጨመረ ጠቅሰው፣ በበርካታ ሥፍራዎች የተከማቸ ውኃ መኖሩንና የጸጥታ ችግርን እንደ ምክንያት አንሥተዋል።

አያይዘውም “የወባ በሽታ መስፋፋት ችግር፣ እንደ ዞናችን የታወቀ ነው። በዞናችን ካለው የመሬት አቀማመጥ እና ውኃ ጋራ ተያይዞ፣ በየዓመቱ ሥርጭቱ ከፍ ያለ ነው። ዘንድሮም በመጠኑም ቢኾን ጨምሯል።” ብለዋል።

በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ 488 የጤና ኬላዎች መካከል፣ በከፊል ጉዳት ስለደረሰባቸው አገልግሎት እየሰጡ እንዳልኾኑ ሓላፊው ጠቅሰው፣ በዞኑ የሚገኙ ስምንት ሆስፒታሎች እና ከ69 ጤና ጣቢያዎች ከሁለቱ በቀር ሌሎቹ፣ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደኾኑ ጨምረው ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UN OCHA)፣ በግጭት ሳቢያ፣ የወባ ትንኝን የሚያጠፋ መድኃኒትን ወደ ወረዳዎቹ ለማሠራጨት ከዞኖቹ ዐቅም በላይ እንደኾነ በሪፖርቱ አትቷል። የሰብአዊ አጋር ድርጅቶችም፣ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለማድረስ የተቸገሩት፣ በግጭት እና መንገድ መዘጋጋት የተነሣ እንደኾነ ይጠቅሳል። ይህም ኾኖ፣ የፀረ ወባ መድኃኒት እና መመርመያ፣ አጎበር እና ፀረ ወባ ኬሚካል እጥረት እንዳለ በመጥቀስ፣ ቁሳቁሶቹን ለማሰባሰብ ቅስቀሳ መደረግ አለበት፤ ሲል በሪፖርቱ አስፍሯል።

በዚኹ ጉዳይ ላይ፣ ከምዕራብ ወለጋ ዞን ውጭ፣ ከሌሎቹ የወለጋ ዞኖች እና ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ባለሥልጣናት፣ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት፣ ለአሁኑ አልተሳካም።

በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሸማቂዎች፣ እንዲሁም በተለያዩ ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች መካከል በሚካሔደው ግጭት፣ የጤና አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎችም መሠረታዊ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች፣ አዳጋች ኹኔታ ላይ እንደደረሱ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ስለ መግለጻቸው፣ በተደጋጋሚ ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG