የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር(UNHCR)፣ “ከአራት ቀናት በፊት፣ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ በግዳጅ እንዲመለሱ ተደርገዋል፤” ስለተባሉት ኤርትራውያን፣ ያልተጣራ መረጃ እንደደረሰው አስታወቀ፡፡
ስደተኞች ያለፈቃዳቸው ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ በቅርበት እየሠራኹ ነው፤ ያለው ተቋሙ፣ እንዲህ ዐይነቱ አድራጎት፣ “ዓለም አቀፍ የስደተኞችን ሕግ ይፃረራል፤” ብሏል፡፡
በጉዳዩ ዙርያ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ ኤርትራውያን ስደተኞች በበኩላቸው፣ ከዐዲስ አበባ፣ በግዳጅ ወደ ኤርትራ የተመለሱት ቤተሰቦቻቸው፣ “ለኤርትራ የጸጥታ ኃይሎች ተላልፈው እንደተሰጡ ሰምተናል፤” ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር(UNHCR)፣ “ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ በግዳጅ እንዲመለሱ ተደርገዋል፤” ስለተባሉት ኤርትራውያን አስተያየት እንዲሰጥ በአሜሪካ ድምፅ ለቀረበለት ጥያቄ በላከው ምላሽ፣ ተቋሙ፥ እንዲህ ዐይነት ያልተጣራ መረጃ እንደደረሰው አስታውቋል፡፡
የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነሩ በኢሜይል ምላሹ፣ “የተወሰኑ ኤርትራውያን ስደተኞች በግዳጅ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል ተብሎ ስለተሠራጨው ያልተጣራ መረጃ አውቃለኹ፤” ብሏል፡፡ “ማንኛውም ስደተኛ፣ ሳይፈልግ ወደ አገሩ እንዳይመለስ ለማረጋገጥ፣ ከሚመለከታቸው የስደተኞች መሪዎች እና ማኅበረሰቦች፣ ከኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት፣ እንዲሁም ከሌሎች መንግሥታዊ አካላት ጋራ በቅርበት እየሠራ” እንደኾነም ኮሚሽነሩ አመልክቷል፡፡ እንዲህ ዐይነቱ ድርጊት፣ ዓለም አቀፍ የስደተኞችን ሕግ የሚፃረር እንደኾነም ጠቅሷል፡፡
ዛሬ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ፣ ማንነታቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን የኤርትራ ስደተኞች ደግሞ፣ ቤተሰቦቻቸው፥ ከአራት ቀናት በፊት፣ ከዐዲስ አበባ ወደ ኤርትራ በግዳጅ እንዲመለሱ መደረጋቸውን ገልጸው፣ አሰብ ከደረሱ በኋላ፣ ለኤርትራ የጸጥታ ኃይሎች ተላልፈው እንደተሰጡ ሰምተናል፤ ብለዋል፡፡ በትናንትናው ዕለት አስተያየት የሰጠን አንድ ማንነቱ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ኤርትራዊ ስደተኛ፣ ከዐዲስ አበባ ተይዘው በግዳጅ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ ከተደረጉት ውስጥ፣ ታናሽ ወንድሙ እንደሚገኝበት ተናግሯል። ወንድሙ የተወሰደው፣ ለአንድ ወር ከሁለት ሳምንት ታስሮ ከቆየ በኋላ እንደኾነም ገልጿል፡፡
“ሕጋዊ የመንቀሳቀሻ ወረቀት የላችኹም፤ ብለው ነው ያሰሯቸው። የወንድሜ የመንቀሳቀሻ ወረቀት አልታደሰም ነበር። በትግራይ በነበረው ጦርነት ምክንያት፣ ከዚያ ተፈናቅለን ከመጣን በኋላ፣ ወረቀታችን አልታደሰም፡፡ ለምን ብትለኝ፣ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት፣ ወረቀት አያድስልንም ነበር፡፡ ስለዚኽ፣ ምንም ማድረግ አልቻልንም፡፡ በዚኽ ምክንያት ተይዞ፣ ለአንድ ወር ከሁለት ሳምንት ያህል ታስሮ ቆይቷል፡፡”
በጉዳዩ ላይ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየቱን የሰጠ ሌላ ኤርትራዊ ስደተኛም፣ “ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ ከተደረጉት ሰዎች መካከል፣ ከልጆቻቸው ተነጥለው የተወሰዱ እናቶች እንደሚገኙባቸው” ጠቅሶ፣ ርምጃው በሌላውም ስደተኛ ዘንድ ስጋት እንደፈጠረ ተናግሯል።
በአሁኑ ጊዜ፣ የኤርትራ ስደተኛ ጭንቀት ውስጥ ነው ያለው። ምክንያቱም፣ ምናልባት አሁን የተጀመረው ኤርትራውያንን የማባረር ድርጊት፣ በቀጣይ ወደ ሌሎቻችንም ይመጣል፤ የሚል ስጋት አለብን። መንግሥት ኤርትራውያንን ከዐዲስ አበባ የማባረሩን ድርጊት ሊቀጥልበት ይችላል፤ የሚል ፍርሃት ይዞናል። አሁን ለተባረሩት ሰዎች፣ ምክንያቱ ምን እንደኾነ፣ ግልጽ አለመኾኑ ደግሞ ስጋታችንን ጨምሮታል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ፣ 200 የሚኾኑ ኤርትራውያን፣ በግዳጅ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጋቸው እንዳሳሰበው አስታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ እንደገለጸው፣ አድራጎቱ፥ “በስደተኞች እና ከለላ ጠያቂዎች ደኅንነት ላይ ስጋት የደቀነ” እንደኾነም አመልክቷል። ችግሩ፣ ከስደተኞች ምዝገባ እና የሕጋዊ ሰነዶች እድሳት አለመኖር ጋራ ተያይዞ የተፈጠረ ስለኾነ፣ አገልግሎቱ ፈጥኖ እንዲጀመርም ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ፣ “ለስደተኞች ደኅንነት እየተወሰደ ነው፤” ያለውንና “ዘርፈ ብዙ” ሲል የጠራውን “ርምጃ ከግምት ያስገባ አይደለም” ብሎታል፡፡ “ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ የተደረጉት ሰዎች፥ ስደተኞችም ጥገኝነት ጠያቂዎችም አይደሉም፤” ያለው የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት፣ ከእነርሱ ጋራ በስሕተት ተወስደው የነበሩ አራት ስደተኞች ግን፣ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ እንደተደረጉ ገልጿል።
ትላንት፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በበኩላቸው፣ ሰዎቹ፣ ስደተኞች አልያም ጥገኝነት ጠያቂዎች ባይኾኑም፣ በግዳጅ መመለስ አልነበረባቸውም፤ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ለስደተኞቹ በግዳጅ መመለስ ምክንያት ሊኾን ይችላል፤ ያለውን፣ የጥገኝነት ጠያቂዎች ምዝገባ እና የሰነድ ማደስ አገልግሎት መቋረጥን በሚመለከት የተጠየቀው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ የዐዲስ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ምዝገባ ከቆመ፣ ሦስት ዓመታትን እንዳስቆጠረ አውስቷል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት፣ ከትግራይ መጠለያ ጣቢያዎች ተፈናቅለው ወደ ዐዲስ አበባ ለገቡ ስደተኞች ግን፣ በኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት፣ የመታወቂያ ሰነድ እንደተሰጣቸው ገልጿል፡፡
ከትግራይ መጠለያ ጣቢያዎች ተፈናቅለው ዐዲስ አበባ ከገቡት 43ሺሕ ስደተኞች፣ 22 ሺሕዎቹ፣ ሕጋዊ ሰነድ እንደተሰጣቸውና በዚኽም የተለያዩ አገልግሎቶችን እያገኙ እንዳሉ፣ አገልግሎቱ በኢሜይል ምላሹ አስፍሯል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት፣ ከሱዳን የተፈናቀሉ 7ሺሕ600 የኤርትራ ስደተኞችን እንደተቀበለችም አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ከዚኽ ቀደም አውጥቶት በነበረ መግለጫ፣ በዐዲስ አበባ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች እና ከለላ ጠያቂዎች፣ “የማስረጃ ሰነድ የላችኹም” በሚል ምክንያት እየታሰሩ እንደኾነ አመልክቶ፣ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ታስረው የሚገኙ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መኖራቸውን ገልጾ ነበር።