በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዓሊዶሮ ከታገቱ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው የማስለቀቂያ ገንዘብ የከፈሉ እንደተለቀቁ ተገለጸ


በዓሊዶሮ ከታገቱ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው የማስለቀቂያ ገንዘብ የከፈሉ እንደተለቀቁ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:14 0:00

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ምዕራብ ሸዋ ዞን “ዓሊደሮ” በተባለ አካባቢ፣ ከሳምንት በላይ ከታገቱ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው መካከል፣ 16 የሚኾኑቱ፣ የተጠየቁትን የማስለቀቂያ ቤዛ(ገንዘብ) ከፍለው መለቀቃቸውን፣ የታጋች ቤተሰቦች ተናገሩ።

ለልጆቻቸው መታገት፣ “ሸኔ” ብለው የጠሩትን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች ተጠያቂ ያደረጉት፣ ልጃቸው ታግቶባቸው የነበሩ አንድ ወላጅ፣ ትላንት ሰኞ፣ አንድ ሚልየን ብር ከፍለው ከእገታው እንዳስለቀቁት ተናግረዋል።

ከታገቱት አሽከርካሪዎች ውስጥ ሰባቱ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ ዐማኑኤል ከተማ ወጣቶች እንደኾኑ የጠቆሙት እኒኽ አባት፣ ከልጃቸው ጋራ አምስቱ እንደተለቀቁ አክለው ገልጸዋል።

ከዐሥር ቀናት በፊት፣ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ “ዓሊዶሮ” በተባለ ቦታ በታጣቂዎች ታግተው ከነበሩ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው መካከል፣ ልጃቸው እንደተለቀቀ፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ የዐማኑኤል ከተማ ነዋሪ የኾኑና ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን አንድ ወላጅ አባት ተናገሩ።

ከዐዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር በሚወስደው መንገድ 149 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው “ዓሊዶሮ” በተባለ ሥፍራ፣ ከዐሥር ቀናት በፊት በታጣቂዎች እንደታገቱ የተነገረውና በቤተሰቦቻቸው 30 ይኾናሉ ተብለው ከተገመቱት አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው መካከል አንዱ ልጃቸው እንደኾነ የጠቀሱት እኚህ አባት፣ የተጠየቀውን የማስለቀቂያ ቤዛ(ገንዘብ) የከፈሉ ታጋቾች እንደተለቀቁ፣ እኚሁ አባት ተናግረዋል።

ከቀናት በፊት ልጃቸው መታገቱንና አንድ ሚሊዮን ብር ቢከፍሉ እንደሚለቁላቸው፣ በስልክ ያነጋገራቸው አካል መኖሩን፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት እኚኹ አባት፣ በተጠየቁት መሠረት ከተለያየ ቦታ ያሰባሰቡትን ገንዘብ፤ “ልክ ከገበያ እንደተመለሰ በማዳበሪያ አስሬ አድርሼ ተመለስኩ” ብለዋል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋራ በተያያዘ ሰኞ፣ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በማቻከል ወረዳ የዐማኑኤል ወረዳ ነዋሪዎች፣ ሰልፍ መውጣታቸውንና ሰልፉን ለመበተን ፖሊስ በወሰደው የኀይል ርምጃ፣ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን፣ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉና በቦታው ነበርኹ ያሉ ግለሰብ፣ ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ግን፣ ሰሞኑን፣ ስለ ጉዳዩ ከአሜሪካ ድምፅ ተጠይቀው፣ ታጣቂዎቻቸው እንዲህ ዐይነቱን ድርጊት እንዳልፈጸሙ ገልጸው፣ በተጠቀሰው አካባቢ፣ የተለያዩ ኃይሎች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተያየታቸውን የሰጡ ሲኾን፣ በኦሮሚያ ክልል እየተባባሰ ለመጣው የሰላማዊ ሰዎች ግድያ እና እገታ መንግሥት ርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሳምንቱ መጨረሻ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ/ኢዜማ/ ባወጣው መግለጫ፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግድያ እና እገታ፣ መንግሥት እንዲያስቆም ጠይቋል፤ ለጥቃቱም፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ተጠያቂ አድርጏል፡፡

ትላንት፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ ቃለ ምልልስ ያደረጉት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ/ኦፌኮ/ ሊቀ መንበር ዶር. መራራ ጉዲና፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ሰለሚፈጸመው ግድያ እና እገታ አስተያየታቸውን ተጠይቀው፣ በድርጊቱ ላይ የተለያዩ አካላት እንደሚሳተፉ ገልጸው፣ ጉዳዩ በገለልተኛ አካላት መጣራት አለበት፤ ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት፣ በጉዳዩ ላይ ያለውን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡

ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

XS
SM
MD
LG