በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቻይና ይገኛሉ


አንተኒ ብሊንከን እና ቻይናው አቻቸው ኪን ጋንግ (ፎቶ ኤፒ ሰኔ 18፣ 2023)
አንተኒ ብሊንከን እና ቻይናው አቻቸው ኪን ጋንግ (ፎቶ ኤፒ ሰኔ 18፣ 2023)

የዩናይትድ ስቴትሱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በቻይና ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ማለዳ ቤጂንግ ገብተዋል። ከአምስት ዓመታት ወዲህ ቻይናን የጎበኙ ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማት ናቸው።

ብሊንከን ከቻይናው አቻቸው ኪን ጋንግ ጋር ተገናኝተው ለ5 ሰዓት ተኩል የቆየ ውይይት አድርገዋል ተብሏል። ውይይቱ በእራት ስነ ሥርዓቱም ላይ እንደቀጠለ ታውቋል።

ብሊንከን በተጨማሪም ከቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋንግ ዪ ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል። እንዲሁም ከቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ሊገናኙ ይችላልም ተብሏል።

ብሊንከን ቻይናን ለመጎብኘት ዕቅድ ይዘው የነበረው ባለፈው የካቲት ሲሆን፣ አንድ የቻይና ሰላይ ፊኛ በአሜሪካ ሰማይ ላይ ሲበር በመገኘቱ ጉብኝታቸውን ለሌላ ግዜ ለማስተላለፍ ወስነዋል።

በሰብአዊ መብት፣ በታይዋን ጉዳይ፣ በቴክኖሎጂ እና ሌሎች የጸጥታ ጉዳዮች ላይ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ በመሆኑ፣ በዚህ ጉብኝት ብዙ የሚጠበቅ ነገር እንደማይኖር ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት “እጅግ አሳሳቢ” የሚሏቸው ጉዳዮችን በተመለከተ ለቻይና ባለስልጣናት በግልጽ እንደሚነግሯቸው ብሊንከን ወደ ቻይና ከማቅናታቸው ቀደም ብሎ ባለፈው ዓርብ ተናግረው ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በመጪው ሐሙስ አሜሪካንን እንደሚጎበኙ የጠበቃል።

በሁለቱ አገራት መካከል በብዙ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ቢኖርም፣ የቻይና በዓለም መድረክ እያየለች መምጣት ግኑኝነታቸውን እንዲያሳልጡ ግፊት አድርጓል ተብሏል።

ለሶስት ዓመታት የዘለቀው፣ በህንድ እና በቻይና መካከል በኢንዶ ፓሲፊክ ላይ ያለው ወታደራዊ ፍጥጫ፣ ሕንድ የአሜሪካንን ርዳታ እንድትሻ ሳያደርግ እንዳልቀረ ይገመታል።

XS
SM
MD
LG