በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የወላዶች ፈተና በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ


የወላዶች ፈተና በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:55 0:00

- መፈናቀል ባስከተለባቸው ፍቺ ለተደራራቢ ችግር እየተዳረጉ ነው

በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የወለዱ እናቶች፥ በአሳሳቢ የምግብ፣ የሕክምና እና የመጠለያ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተናገሩ፡፡

ወይዘሮ ለምለም ወንዳፍራሽ፣ ከምሥራቅ ወለጋ ዞን ሲቡስሬ ከተባለ አካባቢ፣ የስድስት፣ የ10 እና የ14 ዓመት ዕድሜ ካላቸው ሦስት ልጆቻቸው ጋራ ተፈናቅለው፣ ደብረ ብርሃን የደረሱት ፣ በያዝነው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ነው፡፡

የአራት ወር ነፍሰ ጡር ኾነው ከቀዬአቸው የወጡት ወይዘሮ ለምለም፣ አራተኛ ልጃቸውን በደብረ ብርሃን ቻይና መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከወለዱ፣ ገና ሁለት ወራቸው ነው፡፡

ለመውለድ ምቹ ባልኾነ መጠለያ ውስጥ፣ በቂ የምግብ አቅርቦት ሳያገኙ አራስ መኾን ከባድ እንደኾነ፤ ይናገራሉ፡፡ወደ ደብረ ብርሃን ከመምጣታቸው በፊት፣ ሦስት ልጆቻቸውን ሲወልዱ፣ የአራስ ወጉ እንዳልተጓደለባቸው የሚናገሩት ወሮ. ለምለም፣ አሁን ግን ሁሉም ነገር እንደከበደባቸው አልደበቁም፡፡

የሦስት ልጆቻቸው አባት፣ ምሥራቅ ወለጋ ውስጥ በተቀሰቀሰው የጸጥታ ችግር፣ በሰው እጅ ሕይወታቸውን እንዳጡ የሚናገሩት ወሮ. ለምለም፣ የአራተኛ ልጃቸው አባትም፣ መፈናቀሉ ባስከተለባቸው ፈተና ተማርረው፣ ወደማያውቁት ቦታ ጥለዋቸው እንደሔዱ ገልጸዋል፡፡ ይህም፣ የመፈናቀል እንግልት፣ ካደረሰባቸው አካላዊ ጉስቁልና ባሻገር፣ ለሥነ ልቡና ጫና እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡

የወሮ. ለምለም ቅርብ ቤተሰብ እንደኾኑ የሚናገሩት ሚኪያስ ጉርባው፣ ወላዷ፥ በእርግዝናቸው ወቅትም ኾነ ከወለዱ በኋላ፣ አስቸጋሪ ጊዜያትን ማሳለፋቸውን አውስተዋል፡፡

መፈናቀል፣ ለፍቺ ምክንያት እየኾነ እንደመጣ አቶ ሚኪያስ ጠቁመው፣ በዚኽም ዋና ተጎጅዎቹ፣ ሴቶች እና ሕፃናት ናቸው፤ ብለዋል፡፡

ከምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋዩ ጡቃ ወረዳ ልዩ ስሙ መኮፋ ከሚባለው አካባቢ የመጡት ካሳነሽ ሐሰን ደግሞ፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በሽሽት ላይ ባሉበት መንገድ ላይ መውለዳቸውን ይናገራሉ፡፡

እናቶቹ፣ በቂ ምግብ እና መጠለያ አለማግኘታቸው፣ በሕፃናቱ እድገትም ኾነ በእነርሱ ጤና ላይ ተጽእኖ እንዳይፈጥር ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ወ/ሮ ለምለምም ኾኑ አቶ ሚኪያስ፣ በዚኽ ኹኔታ እስከ መቼ ይዘለቃል፤ የሚል ጥያቄም ያነሣሉ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(UN-OCHA)፣ ከአንድ ቀን በፊት ባወጣው ወቅታዊ ሪፖርቱ፣ በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ፣ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እና የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት

የሚያስፈልጋቸው፣ የሚያጠቡ እና ነፍሰ ጡር እናቶች፣ እንዲሁም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ሕፃናት ቁጥር ጨምሯል፡፡ በዚኽም የምግብ ድጋፉ አስፈላጊነት፣ አንገብጋቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ብሏል፡፡

በደብረ ብርሃን ቻይና መጠለያ ካምፕ ውስጥ፣ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡት የጤና ባለሞያው በለጠ ዓለማየሁ፣ ከሳምንታት በፊት ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት አስተያየት፣ ለሕክምና ከሚመጡት አብዛኞቹ፣ የምግብ እጥረት ያለባቸው ሕፃናት እና እናቶች እንደኾኑ ተናግረው ነበር፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ ዞኖች የመጡ፣ 30ሺሕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች፣ በደብረ ብርሃን ውስጥ ባሉ ስድስት መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ፣ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG