በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ግሪክ የሰጠሙ ስደተኞችን የማዳን ጥረቷን ቀጥላለች


ግሪክ የሰጠሙ ስደተኞችን የማዳን ጥረቷን ቀጥላለች
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:10 0:00

ግሪክ የሰጠሙ ስደተኞችን የማዳን ጥረቷን ቀጥላለች

ግሪክ አቅራቢያ በሚገኝ ባህር ዳርቻ፣ ከመጠን በላይ ሰዎችን በመጫኑ ተገልብጦ በሰጠመው ጀልባ ህይወታቸው ያለፈው ስደተኞች ቁጥር 78 የደረሰ ሲሆን፣ አሁንም በመቶዎች የሚቆጠሩ የደረሱበት አልታወቀም።እስከአሁን ወደ 140 የሚጠጉ ስደተኞች በህይወት የተገኙ ሲሆን ተጨማሪ ሰዎችን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ ነው። በቅርብ አመታት ውስጥ ከደረሱ አደጋዎች የከፋ መሆኑ የተገለፀው ይህ አሳዛኝ ክስተት፣ ሊቀለብስ ይችል እንደሆነም ጥያቄዎችን አስነስቷል።

የመርከብ መገልበጥ አደጋው በደረሰበት፣ ከግሪክ በስደቡብ ምስራቅ ከምትገኘው ፓይሎስ ከተማ 80 ኪሎሜትር ርቀት ላይ፣ ስድስት የባህር ዳርቻ ጠባቂ መርከቦች፣ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር እና የባህር ኃይል መርከብ ተሰማርተው ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። በህይወት የተረፉ ሰዎችን የማግኘቱ ተስፋ ግን እየተመናመነ ነው።

እስካሁን ድረስ 140 ስደተኞች በህይወት የተገኙ ሲሆን፣ ሁሉም ወንዶች እና፣ አባዛኞቹ ከግብፅ፣ ከሶሪያ፣ ከፓኪስታን እና ከፍልስጤም የመጡ ናቸው። የአደጋውን አስከፊነት ለማሰብም፣ ግሪክ የሥስት ቀን ብሄራዊ ሐዘን አውጃለች። 30 ሜትር ርዝማኔ ባለው አሳ ማጥመጃ ጀልባ ላይ ተሳፍረው የነበሩ ሰዎች ቁጥር በትክክል ባይታወቅም፣ በህይወት የተረፉት ሰዎች በሰጡት መረጃ መሰረት፣ ምናልባት 750 ሰዎች በመርከቡ ላይ እንደነበሩ ተገምቷል።

ሁኔታውን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ከተሳፋሪዎቹ መካከል 100 የሚሆኑት ሴቶች እና ህፃናት፣ ከመርከቧ የታችኛው ክፍል ተቆልፎባቸው እንዲቀመጡ ተደርጎ የነበር መሆኑ ነው። ህገወጥ አዘዋዋሪዎች ወደ ምዕራቡ ዓለም በሚያደርጓቸው ተመሳሳይ አደገኛ ጉዞዎች ሴቶች እና ህፃናትን የመርከቡ የታችኛው ክፍል ቆልፎ ማስቀመጥ የተለመደ ተግባር መሆነም ተመልክቷል።

ከአቴንስ በስተ ደቡብ ምዕራብ 240 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘው ካላማታ ከተማ ወደብ ላይ ከመርከብ መገልበጥ አደጋ የተረፉ ሰዎች/ረቡዕ፣ ሰኔ 8፣ 2015 ዓ.ም/
ከአቴንስ በስተ ደቡብ ምዕራብ 240 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘው ካላማታ ከተማ ወደብ ላይ ከመርከብ መገልበጥ አደጋ የተረፉ ሰዎች/ረቡዕ፣ ሰኔ 8፣ 2015 ዓ.ም/

የአስከፊው አደጋ መንስዔዎች እየተጣሩ ሲሆን፣ ሐሙስ እለት ባለስልጣናት እንዳስታወቁት፣ ከሊቢያ ተነስቶ ወደ ጣሊያን በመጓዝ ላይ የነበረው ጀልባ ብዙም ርቀት ሳይሄድ በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ሲንሳፈፍ ቆይቷል። የግሪክ የባህር ጠረፍ ጠባቂ ቃል አቀባይ ኒኮስ አሌክሲዮ ስለሁኔታው ሲያብራሩ "ጀልባው ገና ጉዞ እንደጀመረ ሞተሩ ጠፋ። ከመጠን በላይ ሰዎች መርከቡ ላይ ስለተጫኑም፣ የሰዎች እንቅስቃሴ እንዲያዘም እና እንዲገለበጥ አድርጎታል" ይላሉ።

አሌክሲዮ አክለው፣ የባህር ዳርቻ ጥበቃ ከአደጋው በፊት መርከቧን ለማግኘት እና ለመቅረብ ብዙ ሙከራዎችን ማድረጉን ገልፀው፣ ነገር ግን ሁሉም ሙከራ ተቀባይነት አለማግኘቱን አስረድተዋል። "እኛ እነሱ ጋር ከመድረሳችን በፊት ከአንድ የንግድ መርከብ የቀረበላቸውን የምግብ እርዳታ እምቢ ብለዋል። ጣሊያን ለመድረስ የነበራቸው ቁርጠኝነት ግትር አቋም እንዲኖራቸው አድርጓል።"

የግሪክ ፕሬዚዳንት ካትሪና ሳኬላሮፑሉ ከአደጋው ተርፈው፣ ካላማታ በተሰኘች የግሪክ ከተማ ወደሚገኝ መጠለያ የተወሰዱትን ስደተኞች የጎበኙ ሲሆን፣ የከተማዋ ከንቲባ ታናሲስ ቫሲሎፖለስ ስደተኞቹን ለመርዳት የተለያዩ አገልግሎቶች እየቀረቡላቸው መሆኑን ገልፀዋል። "ለሁሉም እንክብካቤ እያደረግን ነው። መጠለያ፣ መፀዳጃ፣ መታጠቢያ እና ሌላም የሚያስፈልጋቸውን አዘጋጅተናል" ያሉት ቫሲሎፖለስ፣ "ለሊቱን እዚህ ሲያሳልፉ የሚበሉት እና ለነገ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት የሚሆን ምግብም መጥቷል" ብለዋል።

ከአራት ዓመት በፊት ስልጣን የያዙት እና እስከቅርብ ጊዜ በግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ኪሪያኮስ ሚትሶታከስ የሚመራው ቀኝ አክራሪ የግሪክ መንግስት ጥብቅ የፍልሰት መቆጣጠሪያዎችን ተግባራዊ አድርጓል። ሆኖም አሌክሲዩ "በግዳጅ ጣልቃ ገብተን ጀልባዋን ወደ ባህር ዳርቻ ለመጎተት ብንሞክር ኖሮ አደጋው ከዚህም በላይ የከፋ ይሆን ነበር። ግሪክም የአደጋው መንስዔ ተደርጋ ትወቀስ ነበር" አደጋውን ማስቀረት ይቻል ነበር የሚለውን ውንጀላ ውድቅ አድርገዋል።

ከመርከብ መገልበጥ አደጋው የተረፉ ሰዎች።
ከመርከብ መገልበጥ አደጋው የተረፉ ሰዎች።

በምትኩ የግሪክ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች ሁኔታውን መከታተል መርጠዋል። አሌክሲዮ እንደሚሉት፣ አደጋው ሲደርስ ጥበቃዎቹ በቅርብ ርቀት ኖረው በፍጥነት እርምጃ ባይወስዱ ኖሮ አደጋው ከዚህም የከፋ፣ በህይወት የተረፉ ሰዎች ቁጥሩም እጅጉን ያነሰ ይሆን ነበር።

የአውሮፓ ህብረት ባለሥልጣናት በተፈጠረው አደጋ ማዘናቸውን ገልፀው፣ ህገወጥ አዘዋዋሪዎችን ለመዋጋት የበለጠ የተቀናጀ ስልት እንዲኖር ጠይቀዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው፣ እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች፣ ፍልሰተኞች ወደ ምዕራቡ ዓለም ለመድረስ የበለጠ አድገኛ የሆኑ መንገዶችን እንዲጠቀሙ እያስገደዳቸው ነው ይላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ በተፈጠረው አደጋ ማዘናቸውን ገልፀው ባወጡት መግለጫ "የተሻለ ሕይወት ለማግኘት የሚፈልግ እያንዳንዱ ሰው ክብር እና ደህንነት ያስፈልገዋል" ያሉ ሲሆን "ይህ አደጋ የመንግስታት ድርጅቱ አባል ሀገራት ተሰብስበው፣ ለመሰደድ የተገደዱ ሰዎች ሥርዓት ባለው እና ደህንነታቸው በተጠበቀ መንገድ የሚተላለፉበትን መንገድ መፍጠር እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንዳመለከተው በዚህ ዓመት ብቻ ከ70 ሺህ በላይ ስደተኞች እንደ ግሪክ፣ ጣሊያን፣ ስፔይን እና ቆፕሮስ የመሳሰሉ በሜድትራኒያን ዳርቻ ላይ የሚገኙ የአውሮፓ ሀገራት ገብተዋል። በተመሳሳይ ዓመትም ወደ አውሮፓ ጉዞ ያደረጉ ወደ 1ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ሰጥመዋል ወይም የደረሱበት አይታወቅም።

//ዘገባውን አንቲ ካራሳቫ ከአቴንስ አጠናቅራዋለች። ስመኝሽ የቆየ ወደ ዐማርኛ መልሳዋለች//

XS
SM
MD
LG