በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለኢትዮጵያ የድኅረ ጦርነት መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ


ለኢትዮጵያ የድኅረ ጦርነት መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:19 0:00

በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ፣ በነበረው ጦርነት እና ግጭት ምክንያት፣ በአገሪቱ ከ22 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጉዳት እና ውድመት መድረሱ ተገለጸ፡፡

የአምስት ዓመት የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ይፋ ሲደረግ እንደተገለጸው፣ የጉዳት እና የመልሶ ማቋቋም ፍላጎት ዳሰሳው፣ በተለያዩ ክልሎች ተካሒዷል፡፡

በሥነ ሥርዐቱ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ዕቅዱን ለማስፈጸም፣ 20ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በሥነ ሥርዐቱ የተሳተፉት የክልል ርእሳነ መስተዳድሮችም፣ በዕቅዱ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት፣ የኢትዮጵያ የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ መርሐ ግብር ይፋ በተደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ የቀረበ አንድ ጥናት እንዳመለከተው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዋናነት በሰሜን ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም በአሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በነበረው ጦርነት እና ግጭት ምክንያት፣ 22ነጥብ 69 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ጉዳት እና ውድመት ደርሷል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ፣ ከዓለም ባንክ እና ከሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ፣ በኢትዮጰያ መንግሥት እንደተደረገ ተገልጿል፡፡ ከዚኽ ጉዳት እና ውድመት ለመውጣት፣ የአምስት ዓመት የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ መርሐ ግብር መዘጋጀቱን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ተናግረዋል፡፡

በሥነ ሥርዐቱ ላይ፣ የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ተወካዮች የተሳተፉ ሲኾን፣ የክልሎች ርእሳነ መስተዳድሮችም ተገኝተዋል፡፡ በመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ መርሐ ግብሩም ላይ አስተየያየት ሰጥተዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፣ በክልሉ የደረሰው ጉዳት እና ውድመት ግዙፍ እንደኾነ ጠቅሰው፣ በዕቅዱ ቅድሚያ ማግኘት አለባቸው ያሏቸውን ተግባራት ሲዘረዝሩ፣ “ጦርነቱ ብዙ ሕይወትን ቀጥፏል፤ በመሠረተ ልማት ላይም መጠነ ሰፊ ውድመትን አስከትሏል፡፡ በትግራይ ግን

ጉዳቱ ከዚያም በላይ ነው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት የክልላዊ መንግሥቱ መዋቅር እንዳለ ነው የፈረሰው፡፡ በአብዛኛው፣ የመንግሥት ተቋማት እንደ ዐዲስ ነው እየጀመሩ ያሉት፡፡ ያሉን የተፈናቃዮች ብዛት አስደንጋጭ ነው፡፡ ልጆቻችን ትምህርት ካቆሙ አራት ዓመታት ኾኗቸዋል፡፡ አርሶ አደሮቻችን የተለመደውን የእርሻ ሥራ ለመከወን የማይችሉበት ኹኔታ ተፈጥሯል፤” ብለዋል።

አክለውም፣ “ለእኛ በዚኽ ሰዓት፣ ስለ መልሶ ግንባታ መናገር ቅንጦት ይኾንብናል፤ ምክንያቱም ከዚያ በፊት፣ በርካታ የማገገሚያ ሥራዎችን ማከናወን አለብን፡፡ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስ አለብን፡፡ አርሶ አደሮቻችን ማረስ እንዲጀምሩ ማስቻል አለብን፡፡ ተማሪዎቻችንን ወደ ትምህርት ቤት መመለስ አለብን፡፡ ቢያንስ እውነተኛውን ትምህርት እንዲያገኙ ሳይኾን፣ እንደው ለስሙ አእምሯቸው ከጦርነቱ ድባብ እንዲርቅ ያህል፤” ብለዋል።

በትግራይ የደረሰው ጉዳት እና ውድመት የተለየ ነው፤ ያሉት አቶ ጌታቸው፣ “በርካታ የቀድሞ ተዋጊዎች አሉን፡፡ እነርሱን በአግባቡ ማቋቋም ካልተቻለ፣ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ማድረግ ያስቸግራል፤ ብለዋል፡፡

በክልሉ ያለው የተረጂዎች ቁጥር፣ ከስድስት ወራት በፊት ከነበረው ስድስት ሚሊዮን፣ ያለምንም ሳይንሳዊ ጥናት ወደ ሦስት ሚሊዮን እንደወረደ ቢገለጽም፣ እነዚኽም ቢኾኑ በአሁኑ ጊዜ፣ ምንም ዓይነት ርዳታ እያገኙ አይደሉም፤ ብለዋል አቶ ጌታቸው፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት፣ በሚቀጥሉት ሦስት እና አራት ወራት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት የቻሉትን ያህል ያግዙን፤ ከዚያ በኋላ ስለ መልሶ ግንባታ እንናገራለን፤ ሲሉም አክለዋል፡፡

የዐማራ ክልል ፕሬዚዳንት ዶር. ይልቃል ከፋለ፣ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በክልሉ የደረሰውን ጉዳት እና ውድመት፣ ሳይንሳዊ በኾነ መንገድ መጠናቱን ተናግረው፣ ውጤቱም ታትሞ እንደተሠራጨ ገልጸዋል፡፡

ክልሉ ከደረሰበት ጉዳት እና ውድመት እንዲያገግምም፣ በመልሶ ማቋቋሙ እና ግንባታ ሒደቱ ተባብረን ልንሠራ ይገባል፤ ሲሉ አመልክተዋል፡፡

በዐማራ ክልል ስላጋጠመው ጉዳት መዘርዘር እንደማይፈልጉ ገልጸው፣ “ጦርነቱ ግን በሰላም ስምምነት ተቋጭቷል፡፡ የዐማራ ክልል እና በጥቅሉ ኢትዮጵያ፣ የሰላም ስምምነቱን ውጤት እያጣጣሙ ናቸው፡፡ አሁን ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ የቀውሱ ዳፋ ግን ቀጥሏል፡፡

መሠረተ ልማት ፈርሷል፤ የጤና እና የትምህርት ተቋማት ወድመዋል፡፡ ጦርነቱ የተካሔደባቸውን አካባቢዎች፣ ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ፣ የጋራ ትብብር እና ቅንጅታዊ አሠራር ይፈልጋል፡፡ በርከት ያለ ገንዘብ ማውጣትን ይፈልጋል፡፡ ይህን ስናደርግ እነርሱም የሰላም ስምምነቱን ውጤት ማጣጣም ይጀምራሉ፡፡ የዘላቂ ሰላም ግንባታ ሒደት አካልም ይኾናሉ፤” ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፣ በደቡባዊ እና ምዕራባዊ የክልሉ አካባቢዎች ያለው ግጭት፣ ከአምስት ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን ጠቅሰው፣ ግጭቱ፥ በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎችም ማኅበራዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ትልቅ ውድመት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ሥራ ለማከናወን፣ በቅድሚያ፣ በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው ሸማቂ ኃይል ጋራ የጀመርነውን የሰላም ጥረት በመቀጠል ከዳር ማድረስ አለብን፤ ብለዋል፡፡ በዚኽ መልኩ፣ ዘላቂ ሰላም ካልተረጋገጠ፣ የመልሶ ግንባታ ጥረቱ እንደማይሳካ አመልክተዋል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ ትላንት እሑድ፣ ሰኔ 4 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ የዐዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለትግራይ ክልል፣ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ርዳታ አድርጓል፡፡ የዐዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ ከ510 ሚሊዮን ብር በላይ የኾነ ድጋፍ፣ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ማስረከባቸውን፣ በመቐለ ከተማ፣ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባትም፣ የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል።

XS
SM
MD
LG