በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በብሊንከን የሳዑዲ ጉብኝት ከእስራኤል ጋራ ያለው ግንኙነት አንዱ አጀንዳ ነው


የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ በደኅንነት እና የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር፣ በዛሬው ዕለት ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቅንተዋል። ብሊንከን፣ ከጉዟቸው አስቀድሞ እንደተናገሩት፣ ዩናይትድ ስቴትስ፥ "በእስራኤል እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል፣ ሰላማዊ ኹኔታን የማራመድ፣ ተጨባጭ የብሔራዊ ደኅንነት ጥቅም አላት፤" ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር አስተዳደር አንሥቶ፥ ግብፅን፣ ባሕሬንን፣ ሞሮኮንና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትን ጨምሮ በበርካታ የአረብ አገሮች እና በእስራኤል መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች ስትሠራ መቆየቷ ይታወቃል።

በሌላ በኩል፣ በዩናይትድ ስቴትስ የእስራኤል ጥቅም ተሟጋቹ “AIPAC” ስብሰባ ላይ ተገኝተው የተናገሩት ብሊንከን፣ የሳዑዲ አረቢያ ጉብኝታቸው፣ የእስራኤልንና የሳዑዲ አረቢያ ግንኙነት ለማጎልበት የሚደረጉ ጥረቶች ያካትታል፤ ብለዋል።

“ይህን ለማራመድ፣ ወሳኝ ሚና መጫወት እንደምንችልና በርግጥም እንደሚያስፈልግ እናምናለን፤" ያሉት ብሊንከን፤ ይኹንና፣ “በፍጥነት ወይም በቀላሉ ሊከናወን ይችላል የሚል ቅዠት ግን የለንም፤” ሲሉ አመልክተዋል።

የብሊንከን የጉብኝት የጊዜ ሰሌዳ፣ ነገ ረቡዕ፣ ከባሕረ ሠላጤው የአረብ አገሮች የትብብር ምክር ቤት ጋራ፥ በደኅንነት፣ በመረጋጋት፣ ግጭቶችን በማርገብ እና ክልላዊ ውሕደትን በሚመለከቱ ጉዳዮች፣ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ አመቺ የምጣኔ ሀብት ዕድሎች ዙሪያ በሚኒስትሮች ደረጃ እንደሚወያዩ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል።

ከነገ በስቲያ ኀሙስ ደግሞ፣ ብሊንከንና የሳዑዲው አቻቸው ፋይሰል ቢን ፋርሃን፣ እስላማዊውን ጽንፈኛ ቡድን አይሲስን በመዋጋት ላይ የሚገኙ 80 አገሮች ያሉበት ጠንካራ ጥምረት የሚሳተፉበትን ስብሰባ፣ በትብብር ያስተናግዳሉ።

XS
SM
MD
LG