በዩክሬይን፣ ባለፉት 48 ሰዓታት፣ ለበርካታ ወራት አንጻራዊ ጸጥታ የነበራቸውን ጨምሮ በበርካታ ግንባሮች፣ ውጊያው እያየለ መምጣቱን፣ የብሪታንያ መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ አስታወቀ፡፡
በሌላ በኩል፣ በጦርነቱ ላይ ዐዲስ ተጨማሪ ቀውስ ላስከተለው ደቡባዊ ዩክሬን ከርሰን አቅራቢያ የሚገኝ አንድ ትልቅ ግድብ ለተናደበት መንሥኤ፣ ዩክሬንና ሩሲያ እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ናቸው።
በሩሲያ ወታደሮች በተያዘው የዩክሬን ግዛት የሚገኘው፣ የኖቫ ካኮቭካ ግድብ መደርመስ ያስከተለው ጎርፍ፣ በዲኒፕሮ ወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ በመቶዎ የሚቆጠሩ ሰዎች፣ አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ማስገደዱ ተዘግቧል። በአቅራቢያው ባሉ ከተሞች የሚገኙ ጎዳናዎች እና አደባባዮች፣ በጎርፉ ተውጠዋል።
ወደ ታች ሲመለከቱ፣ ሩሲያ በስተግራ በኩል የሚገኘውን የወንዙን ዳርቻውንና ግድቡን ስትቆጣጠር፣ ዩክሬን በበኩሏ፣ በስተቀኝ ያለውን የወንዙን ዳርቻ ትቆጣጠራለች።
በሌላ ተያያዥ ዜና፣ በቫቲካን የርእሰ ሊቃነ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ የሰላም መልዕክተኛ ብፁዕ አቡነ ማትዮ ዙፒ፣ “ለትክክለኛ ሰላም” ሲባል የሚያደርጉት ጉብኝት፣ ለችግሩ “ኹነኛ መልሶችን ለማፈላለግ” ይረዳል፤ የሚል ተስፋ እንዳላቸው፣ በቫቲካን የዩክሬን አምባሳደር ተናግረዋል።