በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጀቶች እያሳደዱት በቨርጂኒያ የተከሰከሰው የግል አውሮፕላን ጉዳይ እየተጣራ ነው


ጀቶች እያሳደዱት በቨርጂኒያ የተከሰከሰው የግል አውሮፕላን ጉዳይ እየተጣራ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:32 0:00

ጀቶች እያሳደዱት በቨርጂኒያ የተከሰከሰው የግል አውሮፕላን ጉዳይ እየተጣራ ነው

የዩናይትድ ስቴትስ ፌዴራል መርማሪዎች፣ ትላንት እሑድ፣ ግንኙነት ተቋርጦበት የነበረው ፓይለት፣ በአገሪቱ ዋና ከተማ ሰማይ ከበረረ በኋላ፣ ሁለት ተዋጊ ጀቶች እንዲከተሉት ምክንያት በመኾን፣ በደቡብ ምሥራቅ ቨርጂኒያ ግዛት የተከሰከሰውን የግል አውሮፕላን ኹኔታ ለማጣራት እየሞከሩ ነው፡፡

የቨርጂኒያ ግዛት ፖሊስ፣ አውሮፕላኑ የተከሰከሰበትን አካባቢ በእግር ያሠሡ የነፍስ አድን ሠራተኞች፥ በሕይወት ያገኙት አንድም ሰው አለመኖሩን ተናግሯል፡፡

ከቴነሲ ክፍለ ግዛት የተነሣው አውሮፕላን፣ ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ፊቱን አዙሮ ከመመለሱ በፊት፣ ከታቀደለት የኒዮርክ መዳረሻው ተቃርቦ እንደነበር ተመልክቷል፡፡

የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር፣ አውሮፕላኑ የተከሰከሰው፣ ከዋሽንግተን 200 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ፣ ደቡብ ምዕራብ ቨርጂኒያ ውስጥ በሞንቴቤሎ አቅራቢያ እንደኾነ አስታውቋል፡፡

ቨርጂኒያ ውስጥ፣ በዋና ከተማው አቅራቢያ ሲበር የነበረውን አውሮፕላን ሲያሳድዱ የነበሩት ሁለቱ ተዋጊ ጀቶች፣ እጅግ ከፍተኛ ድምፅ ሲያሰሙ እንደነበር ተነግሯል፡፡

ፌርፋክስ ስቴሽን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ሲያልፉ፣ ይሰማ በነበረው ከፍተኛ የጀቶች ድምፅ በርግጎ የነቃውን ውሻ የሚያሳየው የቪዲዮ ምስል፣ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ከተለቀቁትና እጅግ በርካታ ተመልካቾችን ከሳቡት አንዱ እንደኾነም ተመልክቷል፡፡

የሰሜን አሜሪካ ኤሮስፔስ ኮማንድ ባወጣው መግለጫ፣ ነጎድጓዳዊ ድምፅ ሲያሰሙ የነበሩት ተዋጊ ጀቶቹ፣ ለድምፁ ምክንያት በኾነው “እጅግ ከፍተኛ ፍጥነት እንዲበሩ እንደተፈቀዳላቸው” አስታውቋል፡፡

ጀቶቹ፣ የፓይለቱን ትኩረት ለመሳብ፣ ነበልባላማ ጨረር ሲተኩሱ እንደነበር ተነግሯል፡፡ አውሮፕላኑ፣ በአንኮር ሞተርስ ሜልቦርን ኮርፖሬሽን ስም የተመዘገበ ነው፡፡

ዋሽንግተን ፖስት እና ኒዮርክ ታይምስ፣ የኮርፖሬሽኑ ባለቤት ጆን ረምፔል፣ አውሮፕላኑ፥ የእርሳቸውን ሴት ልጅ፣ የልጅ ልጅ እና ሞግዚቷን ጨምሮ አራት ሰዎችን አሳፍሮ እንደነበር መናገራቸውን ዘግበዋል፡፡

XS
SM
MD
LG