በኬንያ፣ ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ የጤና አገልግሎት ሰጪዎች፣ በቦታው የሚታየው የኮሌራ ወረርሽኝ፣ የከፋ የእልቂት ስጋት እንደጋረጠ ተናገሩ።
የሶማልያ ፍልሰተኞች ቁጥር እየጨመረ ባለበት ሰዓት፣ ለስድስት ወራት የቆየው የኮሌራ ወረርሽኝ፣ እስከ አሁን ከታየው የከፋ እንደኾነ፣ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን(ሜድሳን ሳን ፍሯንትዬር) ገልጿል።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን፣ ትላንት ማክሰኞ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው፣ በኬንያ በሚገኘው የዳዳብ ስደተኞች መጠለያ የተከሠተው የኮሌራ ወረርሽኝ፣ አስጊ ደረጃ ላይ ለመድረስ በመቃረቡ፥ በውኃ እና በንጽሕና አጠባበቅ ረገድ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ማድረግ ያሻል።
“በአካባቢው ያለው ሰብአዊ ኹኔታ የከፋ ነው። እንደ ኮሌራ እና ኩፍኝ ዓይነቱ ወረርሽኝ ሲጨመርበት ይበልጥ ይከፋል። ዛሬ፣ ሰብአዊ ኹኔታው ትኩረት እንዲሰጠው የፈለግነው ለዚያ ነው። ከስድስት ወራት በኋላም ወረርሽኙ ቀጥሏል። ይህ የተለመደ አይደለም፤” በማለት የሚያስረዱት፣ የሕክምና ሥራው አስተባባሪ ዶ/ር ኒትያ ኡዳይራጅ ናቸው።
በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ የስደተኞች መጠለያ በኾነው ዳዳብ፣ የኮሌራ ወረርሽኙ የተከሠተው፣ ባለፈው ኅዳር ወር ነበር። ከዚያ ወዲህ ቢያንስ አምስት ሰዎች፣ በወወርሽኙ ሞተዋል። በዳዳብ መጠለያ፣ 300 ሺሕ ስደተኞች ይገኛሉ። አብዛኞቹ ከጎረቤት ሶማልያ የመጡ ናቸው።
በሶማልያ የሚታየው ድርቅ በመቀጠሉ፣ ወደ ካምፑ የሚመጡት ሰዎች ቁጥር ከይዞታ ዐቅሙ በላይ ነው። ባለፈው ዓመት ብቻ፣ ቢያንስ 67 ሺሕ ተጨማሪ ሰደተኞች ወደ ካምፑ መጥተዋል። ይህም፣ ከመጠለያ ካምፑ ውስን አቅርቦት የተነሣ ጫና ፈጥሯል።
በኬንያ የድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን ሓላፊ ዶ/ር ሓሳን ማያኪ፣ በካምፖቹ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉትን የረድኤት ድርጅቶች በአስረጅነት በመጥቀስ እንደሚናገሩት፣ “በካምፑ ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብ ግማሹ፣ የመጸዳጃ ቤት የለውም። በካምፑ ውስጥ እና በካምፑ ደጃፍ ላይ ነው የሚጸዳዱት፡፡ ይህም የበሽታዎች መከሠት መንሥኤ ይኾናል፡፡”
የኬንያው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ በካምፑ የኮሌራ ክትባት ሰጥቷል። ሐኪሞች እንደሚሉት ግን፣ የንጽሕና መጠበቂያ ኹኔታዎች ካልተሟሉ፣ የኮሌራ ወረርሽኙን ማቆም አስቸጋሪ ይኾናል።