በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቦረና ድርቅ ከትምህርት ያስታጎላቸው ከ2ሺሕ800 በላይ ተማሪዎች አልተመለሱም


በቦረና ድርቅ ከትምህርት ያስታጎላቸው ከ2ሺሕ800 በላይ ተማሪዎች አልተመለሱም
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:14 0:00

ላለፉት ሦስት ዓመታት፣ በቦረና ዞን በተከሠተው ተከታታይ ድርቅ፣ ትምህርታቸውን ከአቋረጡ ተማሪዎች ከ2ሺሕ800 በላይ የኾኑቱ፣ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳልተመለሱ፣ የዞኑ ትምህርት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የቦረና ዞን ትምህርት ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ተስፋዬ ወልደ ሚካኤል፣ ድርቁ በርትቶ በነበረባቸው ወራት፣ ትምህርት ከአቋረጡ ከ7ሺሕ800 በላይ ተማሪዎች ወደ አራት ሺሕ ገደማዎቹ፣ ወደ ትምህርት ገበታ ሲመለሱ የተቀሩት ግን፣ በጋብቻ እና ሌሎች ተጓዳኝ እክሎች ሳይመለሱ መቅረታቸውን አስረድተዋል።

የቦረና ዞን 12ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ ለዘንድሮው መልቀቂያ ፈተና በአግባቡ እንዳይዘጋጁ፣ ድርቁ ዕንቅፋት እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል፡፡

በቦረና ዞን፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ የጣለው ዝናም፣ አካባቢው በልምላሜ እንዲሸፈን ቢያደርግም፣ ነዋሪዎች ላለፉት ሦስት ዓመታት በርትቶ ከሰነበተው ድርቅ ጫና አሁንም አልተላቀቀም። የዞኑን ኢኮኖሚ ክፉኛ ያዳከመው ተከታታይ ድርቅ፣ በመማር ማስተማር ሒደቱ ላይ ያደረሰው አሉታዊ ጫና ከባድ እንደኾነ፣ የቦረና ዞን ትምህርት ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ተስፋዬ ወልደ ሚካኤል ተናግረዋል።

“ባለፉት ዓመታት፣ ለአምስት ተከታታይ የዝናም ወቅቶች፣ ዝናም አልዘነመም ነበር፡፡ ከዚኽም የተነሣ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ቀርተዋል። በተለይ በትምህርት ቤቶች፣ የመጠጥ ውኃ ችግር ነበረ። ከዚኽም የተነሣ፣ በመጀመርያው መንፈቀ ዓመት፣ ከ7ሺሕ800 መቶ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋረጡ። በዚኽ ወቅት፣ በትምህርት ቤቶች የምገባ መርሐ ግብር በፍጥነት ተጀመረ፡፡ ይኹንና፣ ትምህርታቸውን ከአቋረጡ ከ7ሺሕ800 ተማሪዎች መካከል፣ በሕመም፣ በጋብቻ እና በረኀብ፣ 2ሺሕ869 ተማሪዎች ወደ ተማሪ ቤት አልተመለሱም፤ የተቀሩት ግን ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው በመማር ላይ ናቸው።”

ዘንድሮ፣ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ተፈታኙ፣ ሃለኬ ሞሉ ፤ “በፊት በድርቁ ምክንያት፣ ተማሪው በትምህርት ቤት ተገኝቶ ትምህርቱን ለመከታተል አልቻለም፡፡ ያ ኹኔታ በጣም ጎድቶናል። ያለን አማራጭ ትምህርት ብቻ በመኾኑ፣ ለሁለት እና ለሦስት ቀናት ያለምግብ እየቆየንም ቢኾን፣ እርስ በርሳችን እየተደጋገፍን እዚኽ ደርሰናል።’ ይላል።

ደኪ በንት ስላሳለፈችው ጊዜ ስትናገር፤ “የድርቁ ጫና በጣም ከባድ ነው፤ ምክንያቱም እኛን የሚያስተምሩን ቤተሰቦቻችን ናቸው፤ ቤተሰቦቻችን ሀብታቸው ከእጃቸው ካለቀ የምንማርበት አይኖረንም፡፡ በተጨማሪም፣ ቤተሰቦችኽ እየተቸገሩ በክፍል ውስጥ ኾነህ ትምህርት መከታተል በጣም ከባድ ነው።” ብላለች።

በተለይ ከገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማ መጥተው፣ ቤት ተከራይተው ትምህርታቸውን የሚከተታተሉ ተማሪዎች፣ እንዲሁም በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ተገንብተው ባሉ የተማሪዎች ማደርያዎች ወይም(ሆስቴሎች) ያሉ ተማሪዎች የድጋፍ እጥረት እንዳሉባቸው ይናገራሉ።

በያበሎ በሚገኘው የሻለቃ ጃታኒ አሊ ታንዱ መታሰብያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ዳንኤል አኖ፣ “ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎቻችን፣ አጋዥ ወይም የማጠናከሪያ ሥልጠና(Tutorial Class) እየሰጠን ነን፡፡ የልጆቹን ስኬት የሚወዱ፣ ከዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት እና ከቦረና ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ በዚኽ የማስተማር ሥራ እየተሳተፉ ነው፡፡” ይላሉ።

የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አቶ ዋቆ ኩራ፣ ተማሪዎቹ ለዝግጅት ያላቸው ጊዜ አጭር ቢኾንም፣ እያስመዘገቡ ያሉት የክፍል ውጤት መልካም መኾኑን ይናገራሉ።

“በዚኽ ትምህርት ቤት፣ ትልቁን አማካይ ውጤት ያስመዘገበው የ12ኛ ክፍል ተማሪ፣ መለኪያችን ስኩል ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም ነው፡፡ ተማሪዎቻችንን፣ ይህ ሁሉ ጫና ቢደርስባቸውም፣ አንድ የ12ኛ ክፍል ተማሪ፣ ይህን ውጤት ማስመዝገቡ ተስፋ እንዳንቆርጥ ያደርገናል።”

የቦረና ዞን ትምህርት ቢሮ ሓላፊ አቶ ተስፋዬ ወልደ ሚካኤል፣ መንግሥት፣ አሁንም ተማሪዎችን በምገባ መርሐ ግብር ድጋፍ እየሰጣቸው እንደኾነ አስረድተዋል።

“ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ፣ በመጀመርያ ደረጃ፣ ምግብ ማቅረብ ያስፈልጋል። በዞኑ ካሉ 483 ትምህርት ቤቶች፣ በ111ዱ፣ በተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ ርዳታ በመድረስ ላይ ነው፤ በተቀሩት 307 ትምህርት ቤቶች ላይ፣ መንግሥት በራሱ በጀት ምግብ እያቀረበ ነው። ይህም በኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በኩል በጀት ተይዞ፣ ግልጽ ጨረታ ወጥቶ፣ ገዳ ዩኒየን አሸንፎ አሁን ተማሪዎች ምግብ እያገኙ ናቸው።”

የውኃ እጥረቱን አስመልክቶ፣ የዞኑ መጠጥ ውኃ ጽሕፈት ቤት፣ በቦቴ ውኃ ለትምህርት ቤቶች እያቀረበ እንደኾነ አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡ በቦረና የተለያዩ ወረዳዎች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉት የተማሪ ማደርያዎች(ሆስቴሎች)፣ በቁጥር በርከት ያሉ ተማሪዎችን እያስጠለሉ በመኾኑ፣ ወደፊት ሆስቴሎቹን የማስፋፋቱ መርሐ ግብር እንደሚቀጥል፣ የዞኑ የትምህርት ቢሮ ሓላፊ አቶ ተስፋዬ ወልደ ሚካኤል አመልክተዋል።

XS
SM
MD
LG