በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መንግሥት የጎዳና ሕፃናትን “ያለፈቃዳቸው የማንሣት ሕገ ወጥ አሠራሩን” እንዲያቆም ኢሰመኮ አሳሰበ


መንግሥት የጎዳና ሕፃናትን “ያለፈቃዳቸው የማንሣት ሕገ ወጥ አሠራሩን” እንዲያቆም ኢሰመኮ አሳሰበ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:58 0:00

መንግሥት የጎዳና ሕፃናትን “ያለፈቃዳቸው የማንሣት ሕገ ወጥ አሠራሩን” እንዲያቆም ኢሰመኮ አሳሰበ

►የማነሣቸው በዕቅድ እና በፈቃዳቸው ላይ ተመሥርቼ ነው - የዐዲስ አበባ ሴቶች እና ሕፃናት ቢሮ

በዐዲስ አበባ ከተማ፣ የጎዳና ሕፃናትን በኃይል እና በዘፈቀደ እየሰበሰቡ ላይ፣ የመብት ጥሰት እየተፈጸመ እንደኾነ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በአወጣው መግለጫ፣ በከተማዋ፣ የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ እና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በሚኖሩበት ጊዜ፣ የጎዳና ላይ ሕፃናት ከየቦታው ያለፈቃዳቸው እየተሰበሰቡ በጅምላ ተይዘው ወደ ማቆያ ሥፍራ ይወሰዳሉ፤ ብሏል፡፡ ይህ ኹኔታ፣ የሰብአዊ መብቶቻቸውን የሚጥስ እና የሕግ መሠረት የሌለው እንደኾነም፣ በኮሚሽኑ የክትትል እና ምርመራ ዲሬክተር ሰላማዊት ግርማይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡ እንዲህ ዐይነት የኃይል፣ የዘፈቀደ እና ሕገ ወጥ አሠራር ሊወገድ እንደሚገባውም፣ ኮሚሽኑ በመግለጫው አሳስቧል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጠው፣ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የዚኽ ዐይነቱ አካሔድ ተቀባይነት እንደሌለው ሲገልጽ፤ የዐዲስ አበባ የሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ደግሞ፣ ዜጎችን ከጎዳና ላይ የማነሣው በፈቃዳቸው ነው፤ ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአወጣው መግለጫ፣ በዐዲስ አበባ ከተማ፣ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ፤ እንዲሁም በመዲናዋ የሚደረጉ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ጉባኤዎች ሲኖሩ፤ በርካታ የጎዳና ላይ ሕፃናት፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሚያድሩበት ቦታ እንዲነሡ በማድረግ ወደ ማቆያ ሥፍራዎች ይወሰዳሉ፤ ይላል፡፡ ይህ የሚደረገውም፣ የሕፃናቱን መብት በጣሰ አኳኃን መኾኑን፣ በኮሚሽኑ የክትትል እና ምርመራ ክልላዊ ዲሬክተር ሰላማዊት ግርማይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በተለያዩ ጊዜያት የቀረቡለትን ጥቆማዎች መሠረት በማድረግ በአደረገው ክትትል፣ ቁጥራቸው ከ5ሺሕ እስከ 7ሺሕ የሚደርሱ ሕፃናት፣ በከተማዋ የጸጥታ ኃይሎች፣ ከጎዳና ላይ በሌሊት ታፍሰው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኝ የተሐድሶ ማእከል ውስጥ ተይዘው መቆየታቸውን አረጋግጫለኹ፤ ብሏል፡፡ በዚኽ ማዕከል ውስጥ ያለው የአያያዝ ኹኔታቸውም ጉድለት እንዳለበት፣ የክትትል እና ምርመራ ዲሬክተሯ ሰላማዊት ግርማይ ጠቅሰዋል፡፡

ከነሐሴ 2014 እስከ ጥር 2015 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ፣ በዐዲስ አበባ ከተማ፥ የጎዳና ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 14ሺሕ ሰዎች ከጎዳና ላይ በጸጥታ ኃይሎች በግድ ታፍሰዋል፤ ይላል ኮሚሽኑ። የአሜሪካ ድምፅ ስለዚኽ ጉዳይ፣ የዐዲስ አበባ ከተማ የሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮን ጠይቋል፡፡

የቢሮው ምክትል ሓላፊ ወ/ሮ ገነት ቅጣው በሰጡት አስተያየት፣ ቢሮው የጎዳና ላይ ሕፃናትን ጨምሮ የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎችን የሚያነሣው በዕቅድ ነው፤ ሒደቱም በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ብለዋል፡፡

ከዐዲስ አበባ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም። የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን፣ የዚኽ ዐይነት አካሔድ ተገቢ እንዳልኾነ አመልክቷል፡፡ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶር.)፣ በሌላ መድረክ ላይ፣ ስለ ጉዳዩ በአሜሪካ ድምፅ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ የጎዳና ላይ ሕፃናት ያለፈቃዳቸው መነሣት የለባቸውም፤ ብለዋል፡፡

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሕፃናትን ጨምሮ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመርዳት፣ የተለያዩ የማኅበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞችን ቀርፆ እየሠራ እንደኾነና ችግሩን በተቀናጀ መልኩ ለመፍታትም፣ የማኅበራዊ ጥበቃ ፈንድ ለማቋቋም መታቀዱን፣ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የክትትል እና ምርመራ ዲሬክተር ሰላማዊት ግርማይ በበኩላቸው፣ መንግሥት፣ የጎዳና ላይ ሕፃናትን በተመለከተ በሚሠራው ሥራ ሁሉ፣ ሰብአዊ መብቶቻቸውን እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ 150ሺሕ የሚገመቱ የጎዳና ላይ ሕፃናት እንዳሉ የጠቀሰው የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መግለጫ፣ ከእኒኽም ውስጥ፣ ወደ 60ሺሕ የሚደርሱት፣ በዐዲስ አበባ ከተማ እንደሚገኙ ይገመታል ይላል፡፡

XS
SM
MD
LG