በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢራን በሶስት ግለሰቦች ላይ የሞት ቅጣት ተፈጻሚ አደረገች 


የኢራን ካርታ
የኢራን ካርታ

ባለፈው ዓመት በነበረው ጸረ-መንግስት ተቃውሞ ተሳትፈዋል የተባሉ ሶስት ግለሰቦች ላይ ኢራን ዛሬ ዓርብ የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ አድርጋለች፡፡

ሚዛን የተሰኘው የአገሪቱ ፍትህ መ/ቤት ድህረ-ገጽ እንዳስታወቀው፣ ማጂድ ካዜሚ፣ ሳለህ ሚርሃሸሚ፣ እና ሳይድ ያጎቢ በተባሉት ግለሰቦች ላይ የሞት ቅጣቱ ተፈጻሚ ተደርጓል። ሰዎቹ በምን መንገድ እንደተገደሉ ግን አልተገለጸም።

ሶስቱ ግለሰቦች፣ አንድ የፖሊስ አባልንና ሁለት የጸጥታ ጠባቂዎችን ገለዋል ሲሉ ባለሥልጣናት ይከሳሉ።

በሌላ በኩል፣ ሶስቱ ግለሰቦች ላይ ሰቆቃ ተፈጽሟል፣ ፈጸሙ የተባለውን ወንጀል በቴሌቭዥን ቀርበው በግዴታ እንዲያምኑ ተደርጓል፣ እንዲሁም በሕግ ሂደት የመዳኘት መብታቸው ተገፏል ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይከሳሉ።

በአገሪቱ ከተደረገው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ኢራን እስከ አሁን 7 ሰዎች ላይ የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ አድርጋለች፡፡

ማሻ አሚኒ የተባለች የ22 ዓመት ወጣት፣ ሂጃብ በሚገባ አልለበሽም በሚል በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ሳለች ሕይወቷ ማለፉን ተከትሎ ባለፈው መስከረም የተቀሰቀሰው አመጽ አሁን ጋብ ያለ ቢመስልም፣ አልፎ አልፎ ግን ተቃውሞዎች ይስተዋላሉ። በእስልምና እምነት ግዴታ የሆነውን ሂጃብ ባለመልበስ፣ በርካታ ሴቶች በመንግስት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በማሳየት ላይ ናቸው።

XS
SM
MD
LG