በግዳጅ ተፈናቅለው ወደ ሩሲያ ስለሚወሰዱ በ10 ሺሕዎች የሚቆጠሩ የዩክሬን ሕፃናት ርምጃ እንዲወሰድ፣ የመብት ተሟጋች ቡድኖች ጠይቀዋል። ለአንዳንድ የዩክሬን ቤተሰቦች ግን፣ ይህ ዐይነቱ ክሥ፥ በጦርነቱ ውስጥ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ከሚያልፉባቸው በርካታ ውስብስብ ጥቃቶች አንዱ ብቻ ነው። የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ሄዘር መርዶክ ያጠናቀረችውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
እ.አ.አ. በየካቲት 2022 ዓ.ም፣ ሩሲያ፥ በዩክሬን ካርኪቭ ግዛት ውስጥ የምትገኘውንና ኢሪና ግሪንቼንኮ የምትኖርበትን ከተማ ምሽቱን ተቆጣጠረች። ግሪንቼንኮ ኹኔታውን ስታስታውስ፣ “ከእንቅልፋችን ስንነቃ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ነበርን፤” ትላለች።
ጦርነቱ ቀጠለ፤ የሩሲያ ባለሥልጣናትም፣ ሕፃናት፥ በፀሐይ ብርሃን መጫወት እና መማር ወደሚችሉበት ቦታ እንደሚወሰዱ፣ ለወላጆቻቸው ነገሯቸው።
ግሪንቼንኮ በወቅቱ የተሰማትን ስትገልጽ፣ “መጀመሪያ ላይ ልጆቼ፣ ለረጅም ጊዜ ባሕር አይተው አያውቁም ብዬ አሰብኹ። ከጦርነቱ ትንሽ እንዲያርፉና ዐዲስ ጓደኞች እንዲያፈሩም ፈለግኹ፤” ትላለች።
ግሪንቼንኮ ያሰበችው፣ ልጆቹ ለ24 ቀናት እንደሚሔዱ ነው፤ ነገር ግን ሳምንታት ወደ ወራት ተቀየሩ። በሌላ ጊዜ፣ አንድ ቀን ጠዋት ስትነቃ ደግሞ፣ ዩክሬን ከተማዋን በድጋሚ ተቆጣጥራ አገኘችው። ያ ማለት፣ ዐዲሱ ደንበር ተገፍቶ እርሷ እና ልጆቿ በተለያዩ ሀገራት ነው ያሉት።
“በፖላንድ ያሉ ዘመዶቻችን፣ ስለ ኹኔታው የነበራቸው ሐሳብ መጥፎ ነበር፤” የምትለው ግሪንቼንኮ፣ “አሁኑኑ ካላመጣችኋቸው መቼም አታገኟቸውም፤ ይሉን ስለነበር፣ ልጆቹ ወደ ዩክሬን መመለስ አይችሉም፤ ብለን ፈርተን ነበር፤” ስትል፣ ልጆቿን ከሩሲያ ማውጣት እና መልሳ ማግኘት የምትችል እንዳልመሰላት ትገልጻለች።
ግራንቼንኮ፥ “ሴቭ ዩክሬን” ወይም “ዩክሬንን እናድን” የተሰኘ ተቋምን ተማፀነች፡፡ ይህ ተቋም፥ ወላጆች፣ እጅግ ረጅም እና ውስብስብ በኾነ መንገድ፣ ከዩክሬን ወደ ሩሲያ ተጉዘው ልጆቻቸውን እንዲያስመልሱ የሚያግዝ ነው፡፡
የዩክሬን ባለሥልጣናት እንደሚሉት፣ ሩሲያ፥ ከ19ሺሕ በላይ የሚኾኑ ሕፃናትን፣ በቁጥጥር ሥር ይዛቸው ከነበሩ ወይም አሁን ከያዘቻቸው የዩክሬን ከተሞች ወስዳለች። ዓላማቸውም፣ “ልጆቹን በርእዮተ ዓለም ማጥመቅ እና ማንነታቸውን ማጥፋት ነው፤” ይላሉ። ሚኮላ ኩሌባ፣ የ “ዩክሬንን እናድን” ተቋም ሓላፊ ሲኾኑ፣ የሚወሰዱት ሕፃናት፥ የሩሲያን ዘፈኖች እንዲዘፍኑ፣ የሩሲያን ብሔራዊ መዝሙር እንዲዘምሩ እና ወደ ሩሲያ ትምህርት ቤቶች ለመሔድ እንደሚገደዱ እንዲህ ያስረዳሉ፤
“በግዳጅ የተለየ አስተሳሰብ እንዲዘልቃቸው ያደርጋሉ። ዘወትር ስለ ዩክሬን መጥፎ ነገር እየነገሯቸው፣‘መቼም ወደዚያ አትመለሱም፤ ዩክሬን ውስጥ ወላጆቻችኹንና አገራችኹን ጨምሮ ማንም አይፈልጋችሁም። ያን እርሱትና የሩሲያ ዜግነት እንሰጣችኋለን፤ እዚኽ ደስተኛ ትኾናላችኹ፤' ይሏቸዋል።”
በመጋቢት ወር፣ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፣ በሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንና የሩሲያ የሕፃናት መብት ኮሚሽነር በኾኑት ማሪያ ላቮቫ-ቤሎቫ ላይ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ልጆችን ወደ ሩሲያ በመውሰድ ክሥ መሥርቶባቸዋል። ላቮቫ-ቤሎቫ ግን፣ ሕፃናቱን ከጦርነት ለማዳን፣ ከሰብአዊነት አኳያ መወሰዳቸውን በመግለጽ፣ የቀረበባቸውን የወንጀል ክሥ፥ “ሤራ” ሲሉ ገልጸውታል።
ሕፃናቱ የተወሰዱት ለደኅንነታቸው ሲባል እንደኾነ በማመልከት፣ ሞስኮ ልጆችን በመጥለፍ የሚቀርብባትን ክሥ አትቀበልም። ላቮቫ-ቤሎቫም፣ ሕፃናትን ከግጭት አካባቢዎች የማውጣቱን ሥራ እንደሚቀጥሉበት አስታውቀዋል።
ወደ ዩክሬን ለሚመለሱ ልጆች፣ ወደ ቤታቸው በመመለሳቸው ደስታም፣ ኀዘንም የተቀላቀለበት ድብልቅልቅ ስሜት ይፈጥርባቸዋል። የ12 ዓመት ልጅ የኾነችው ናስቲያ፣ ወደ አደገችበት ግሪንቼንኮ ስትመለስ፣ “ይህን ያህል ውድመት አያለኹ ብዬ አልጠበቅኹም ነበር፤” በማለት በጠበቃት የከተማዋ ጥፋት ማዘኗን ትናገራለች። በሩሲያ የነበሩ አስተማሪዎቿ መልካም እንደነበሩና ስለ አካባቢው ታሪክ እንዳስተማሯቸው፣ በሀገራቸው ስላለው ጦርነት ግን እንዳልነገሯቸው ትገልጻለች።
የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት፣ በሚያዝያ ወር መጨረሻ በአወጣው የውሳኔ ሐሳብ ረቂቅ፥ አሳዳጊ አልባ እና አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን፣ ከወላጆቻቸው ጋራ የተወሰዱ ሕፃናትንና ለዕረፍት ተወስደው ያልተመለሱ ልጆችን ጨምሮ፣ በግዳጅ ከዩክሬን ወደ ሩሲያ በሚወሰዱ ሕፃናት ጉዳይ ተጠያቂ የማድረግ ርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል።
/ሄዘር መርዶክ ያጠናቀረችውን ዘገባ ስመኝሽ የቆየ ወደ አማርኛ መልሳዋለች/