በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቱርክ ምርጫ ወደ ድጋሚ ማጣሪያ ያመራል


ፕሬዚዳንት ረችፕ ታይፕ ኤርዶዋን (ፎቶ ኤ ኤፍ ፒ)
ፕሬዚዳንት ረችፕ ታይፕ ኤርዶዋን (ፎቶ ኤ ኤፍ ፒ)

በቱርክ የተካሔደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጀመሪያው ዙር ቆጠራ ውጤት፣ ወደ ድጋሚ የማጣሪያ ምርጫ እንደሚያመራ በማመልከት ላይ ይገኛል፡፡

የምርጫው ሒደት ይህን ቢያመለክትም፣ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን በአሸናፊነታቸው እንደሚተማመኑ ዛሬ ሲያስታውቁ፤ ተፎካካሪያቸው ከማል ኪሊችዳሮግልም፣ “ሁለተኛውን ዙር እንደማሸንፍ ርግጥ ነው፤” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በአገሪቱ ዘመናዊ ታሪክ፣ ለረጅም ጊዜ በመሪነት የቆዩትና ላለፉት 20 ዓመታት የመንግሥቱን ሥልጣን የተቆጣጠሩት ኤርዶዋን፣ ከተጠበቀው የተሻለ ውጤት ቢያስመዘግቡም፣ 50 በመቶ ድምፅ ሳያገኙ ቀርተዋል።

እስከ አሁን ከተጣለው ድምፅ 99ነጥብ 4 በመቶው መቆጠሩ ሲታወቅ፣ ኤርዶዋን 49ነጥብ 4 በመቶ ድምፅ አግኝተዋል፤ ተቀናቃናቸው ከማል ደግሞ፣ 45 በመቶውን እንዳገኙ ታውቋል።

ከቱርክ ውጪ በኾኑ ሀገራት የተሰጡ የዜጎች ድምፆች፣ ገና አልተቆጠሩም፡፡ የድጋሚ ማጣሪያ ምርጫው፣ ግንቦት 20 ቀን እንደሚደረግ ተመልክቷል።

በአገር ውስጥ እና በውጭ፣ 64 ሚሊዮን የሚኾኑ ቱርካውያን ለመምረጥ ብቁ ሲኾኑ፣ ከእነዚኽ ውስጥ 89 በመቶው ድምፅ መስጠታቸውን፣ የአሶሺዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG