በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኤርትራው ፕሬዚዳንት በቤጂንግ ጉብኝት ላይ ናቸው


ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊ ቻንግ (ፎቶ ሮይተርስ ግንቦት 15፣ 2015)
ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊ ቻንግ (ፎቶ ሮይተርስ ግንቦት 15፣ 2015)

“ቻይና እና ኤርትራ፣ ሁለቱም አሸናፊ የሚኾኑበትን ትብብር ማጠናከር እና ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን ማጎልበት አለባቸው፤” ሲሉ፣ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊ ቻንግ፣ አገራቸውን በመጎብኘት ላይ ለሚገኙት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ ተናግረዋል፡፡
በቤጂንግ ከ ሊ ቻንግ ጋራ የተወያዩት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ በበኩላቸው፣ “በአጠቃላይ በዓለም ያለውን ሥርዓት ወደተሻለ እና ፍትሐዊ ግንኙነት ለመቀየር፣ የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ አስተዋፅኦ፣ ሌሎችን የሚያደፋፍር ነው፤” ብለዋል፡፡
ቻይና በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተጽእኖ ለማሳደግ በምትጥርበት ወቅት፣ በቀይ ባሕር ላይ የምትገኘው ኤርትራ ያላት መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ሳቢ ነው፡፡ ሀገረ ኤርትራ፣ በሰሜን ለስዊዝ ካናል እና ለአውሮፓ፣ እንዲሁም በደቡብ ምሥራቅ ከአረብ ባሕረ ሠላጤ እና ከሕንድ ውቅያኖስ ያላት ቅርበት ለቻይና አማላይ ነው። ከስድስት ዓመታት በፊት ወታደራዊ መደብ ያቋቋመችባት ጅቡቲ፣ ከኤርትራ ጋራ መዋሰኗም ለቻይና ሌላው ሳቢ ጉዳይ ነው።
ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ ወደ ቤጂንግ ያመሩት፣ በቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ግብዣ ነው። ሁለቱ መሪዎች፣ በዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉና በጋራ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፤ ሲል፣ የቻይናው ዓለም አቀፍ የቴሌቭዥን አውታር(ሲሲቲቪ) ዘግቧል።
ሁለቱ መሪዎች፣ የሀገራቱን ግንኙነት ለማሳደግ፣ ባለፈው ዓመት መስማማታቸው ይታወሳል፡፡ ቻይና በምትገነባው ግዙፉ አህጉር ዘለል የመቀነት መንገድ ፕሮዤ(Belt and Road Initiative) ላይ ኤርትራ ተሳታፊ ናት፡፡
ባለፈው መጋቢት፣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኤርትራ፥ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሔደው ግጭት የጦር ወንጀል ፈጽማለች፤ ማለቷን፣ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ “ያልተረጋገጠና ስም ማጥፋት” ሲል ገልጾታል።
“የተገለለችው የአፍሪካ አህጉር እና ቀሪው ዓለም፣ ከቻይና ብዙ አስተዋፅኦ ይጠብቃል፤ ሚናዋንም ይደግፋል፤” ብለዋል፣ ቤጂንግ የሚገኙት የሀገረ ኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ።
ቻይና እና ኤርትራ፣ ኦፌሴልያዊ ግንኙነት ከጀመሩ 30 ዓመት ሞልቷቸዋል።
በቅርቡ፣ በሱዳን ባለው ግጭት ምክንያት፣ ከዚያች አገር፣ በመጀመሪያው ዙር የወጡ የቻይና ዜጎች ያቀኑት ወደ ኤርትራ ነበር፡፡

XS
SM
MD
LG