በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትግራይ ክልል ሥርጭቱ የተቋረጠው የሕይወት አድን ርዳታ እንዲቀጥል ጠየቀ


የትግራይ ክልል ሥርጭቱ የተቋረጠው የሕይወት አድን ርዳታ እንዲቀጥል ጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:58 0:00

በአሁኑ ወቅት ወደ ትግራይ ክልል እየገቡ የሚገኙ መጠነኛ አልሚ ምግቦች እና የግብርና ግብኣቶች ቢኖሩም፣ ተቋርጦ የሚገኘውን የሕይወት አድን የርዳታ ምግብ ሥርጭት ማስቀጠሉ የቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ የክልሉ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) በአወጣው ሪፖርት፣ ሁለት ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች፣ በትግራይ ክልል የሚያደርጉትን የርዳታ እህል ሥርጭት በጊዜያዊነት ቢያቋርጡም፣ አልሚ ምግቦች እና የግብርና ግብኣቶች ወደ ክልሉ በመግባት ላይ መኾናቸውን ገልጿል፡፡

በርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮው ሪፖርት ላይ የአሜሪካ ድምፅ አስተያየቱን የጠየቀው የክልሉ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በበኩሉ፣ አልሚ ምግቦቹ እና የግብርና ግብአቶቹ በመግባት ላይ መኾናቸውን ቢያረጋግጥም፣ በመጠን ውሱን እንደኾኑና ከእነርሱም ይልቅ፣ ሥርጭቱ የተቋረጠው የሕይወት አድን የርዳታ ምግብ በአስቸኳይ የሚቀጥልበት ኹኔታ እንዲመቻች ጠይቋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ(OCHA) ባወጣው ሪፖርት፣ በክልሉ፣ የርዳታ እህል ሥርጭት በጊዜያዊነት እንዲቆም ቢደረግም፣ አልሚ ምግቦች እና የግብርና ግብኣቶች እየገቡ እንደኾነና እስከ አሁን ድረስ፣ 1ሺሕ200 ሜትሪክ ቶን ማዳበርያን ጨምሮ ምርጥ ዘር፣ የግብርና ኬሚካል፣ እንዲሁም 26 ትራክተሮች መቐለ መድረሳቸውን አስታውቋል፡፡

በሪፖርቱ ላይ የአሜሪካ ድምፅ ማብራርያ የጠየቃቸው፣ በትግራይ ክልል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ግብረ መልስ ዳይሬክቶሬት ዲሬክተር አቶ ገብረ እግዚአብሔር አረጋዊ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ጊዜ ቅድሚያ መሰጠት የሚኖርበት፣ ለአስቸኳይ ምግብ ፈላጊዎች ሊደርስ የሚገባው የሕይወት አድን የምግብ ርዳታ እንደኾነ ተናግረዋል::

በአሁኑ ወቅት፣ ወደ ክልሉ እየገቡ ናቸው የተባሉት አልሚ ምግቦች እና የግብርና ግብአቶችም ቢኾኑ በጣም ውስን እንደኾኑ፣ አቶ ገብረ እግዚአብሔር ገልጸዋል::

እስከ አሁን፣ “ወደ ክልሉ የገባ ምርጥ ዘር ይኹን የግብርና ኬሚካል የለም፤” ያሉት ዲሬክተሩ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የላከው ድጋፍ ግን፣ ወደ ትግራይ እየተጓጓዘ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ወደ ክልሉ ገብተዋል የተባሉ ትራክተሮችም፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተገዙ ናቸው፤ ሲሉ ተናግረዋል::

እንደ ተመድ የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ(OCHA) ሪፖርት፣ በትግራይ ክልል ሲሠራጭ የቆየው ሰብአዊ ድጋፍ በጊዜያዊነት እንዲቋረጥ ከተደረገ በኋላ ሁለት ዐበይት ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ የርዳታ ምግብን ለሽያጭ በማዋል ተፈጽሟል የተባለውን ምዝበራ፣ የመመርመር እና የማጣራት ሥራ ሲኾን፤ ሌላው ደግሞ፣ በሰብኣዊ ድጋፍ ላይ የሚሠሩ ተቋማት፣ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ጋራ በመቀናጀት፣ ርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች፣ የመለየት እና የመመዝገብ ሥራ እየተፈጸመ መኾኑን፣ የማስተባበሪያ ቢሮው በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

በዚኽም፣ የርዳታ እህሉ ለትክክለኞቹ ተረጂዎች መድረስ እንደሚችል በማረጋገጥ፣ የማከፋፈል ሥራው ዳግም እንደሚጀመር ቢሮው አመልክቷል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ ተራድኦ ተቋም(USAID)፣ ለክልሉ ችግረኞች በሚቀርበው የሕይወት አድን የምግብ ርዳታ ላይ ምዝበራ ተፈጽሟል በሚል፣ በትግራይ ክልል ሲያደርጉ የቆዩትን የነፍስ አድን የምግብ ርዳታ ሥርጭት፣ በጊዜያዊነት ማቆማቸውን፣ ባለፈው ሳምንት በይፋ ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG