በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ሊነጋገሩ ነው


ካርቱም (ፎቶ ኤፒ ግንቦት 3, 2023)
ካርቱም (ፎቶ ኤፒ ግንቦት 3, 2023)

የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመነጋገር ልዑኮቻቸውን ወደ ሳዑዲ አረቢያ መላካቸው ተነግሯል።

የሁለቱም ወገኖች የልዑካን ቡድን አባላት ጀዳ መግባታቸውን የሳዑዲና የአሜሪካ ባለስልጣናት አረጋግጠዋል።

ከዚህ በፊት የተደረጉ የተኩስ ማቆም ስምምነቶች በተደጋጋሚ መክሸፋቸው ይታወሳል።

በጀዳ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ ዛሬ ይደረጋል የተባለው የፊት ለፊት ንግግር በሱዳን እየተደረገ ያለውን ግጭት ለማቆም ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ጥረት ከተደረገ በኋላ የመጣ ነው ተብሏል።

በጀዳ የሚካሄደው ንግግር በሳዑዲ ዓረቢያና በአሜሪካ አሰናጅነት የሚካሄድ ነው ሲሉ የሱዳን ባለሥልጣናት ለአሶስዬትድ ፕረስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

በካርቱምና በኦምዱርማን የሰብዓዊ መተላለፊያ መክፈት፣ የጤና ተቋማትን ጨምሮ የሲቪል መሠረተ ልማቶችን ከጥቃት መጠበቅ፣ በንግግሩ ዋና አጀንዳ ይሆናሉ ሲሉ የሱዳን ባለሥልጣናት ጨምረው ገልጸዋል።

የሁለቱ ተቀናቃኝ ጀኔራሎች ማለትም የአገሪቱ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጀኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን እና ኼመቲ በመባል የሚታወቁት የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ጀኔራል ሞሃመድ ሃምዳን ደጋሎ ተወካዮች ጦርነቱ ከጀመረበት ሚያዚያ 7 ወዲህ ፊት ለፊት ሲገናኙ የዛሬው የመጀመሪያ ነው ተብሏል።

በሱዳን እየተካሄደ ባለው ግጭት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለው ደግሞ፣ 334 ሺህ ሰዎች በአገር ውስጥ ሲፋናቀሉ፣ ከመቶ ሺህ በላይ ሠዎች ደግም አገሪቱን ጥለው ወደ ጎረቤት አገራት ሸሽተዋል።

XS
SM
MD
LG