በትግራይ ክልል ሲከናወን የቆየው የርዳታ ምግብ ሥርጭት እንዲቆም ከተወሰነ 20 ቀናት መቆጠራቸውን፣ የክልሉ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡ ለሥርጭቱ መቆም መንሥኤ ነው የተባለው የርዳታ እህል ሽያጭንም፣ ለማስቆም እየተሠራ መኾኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም(WFP)፣ በክልሉ ለርዳታ በተለገሰው ምግብ ላይ የተፈጸመውን ምዝበራ ለማጣራት የያዘውን የውስጥ ምርመራ እያካሔደ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል የሚያሠራጨውን የርዳታ ምግብ ሥርጭት ማቋረጡን፣ አሶሽየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል መዘገቡ ይታወቃል::
በክልሉ፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ግብረ መልስ ዳይሬክቶሬት ዲሬክተር አቶ ገብረ እግዚአብሔር አረጋዊ፣ የክልሉ አስተዳደር ሲቆጣጠራቸው በነበሩ አካባቢዎች፣ የተዘረፈ የርዳታ እህል የለም፤ በማለት አስተባብለዋል::
አሶሽየትድ ፕረስ የዜና ወኪል ባወጣው ዜና፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም (WFP)፣ ለረኀብ ለተጋለጡ ሰዎች በተለገሰ የርዳታ ምግብ ላይ የተፈጸመውን ምዝበራ ለማጣራት የያዘውን የውስጥ ምርመራ እያካሔደ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ በትግራይ ክልል የሚያካሒደውን የርዳታ ምግብ ሥርጭት ማቋረጡን፣ ከአራት የረድኤት ሠራተኞች ያገኘውን መረጃ መሠረት በማድረግ ዘግቧል፡፡
በዚኹ ጉዳይ ላይ፣ በዛሬው ዕለት በትግራይ ክልል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ግብረ መልስ ዳይሬክቶሬት ዲሬክተር አቶ ገብረ እግዚአብሔር አረጋዊ፣ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራርያ፣ ወደ ክልሉ የነፍስ አድን የርዳታ እህል መግባት እንዲቆም ከተወሰነ 20 ቀናት ማለፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ጦርነቱ በነበረባቸው የተለያዩ ጊዜያት፣ የርዳታ እህሎች መዘረፋቸውን ተናግረዋል፡፡
“በመጀመርያ የጦርነቱ ጊዜያት፣ የርዳታ እህል የተከማቸባቸው ብዙ መጋዘኖች ተዘርፈዋል፡፡ዛላንበሳ፣ ኩለመኸዳ፣ ዓዲግራት፣ ኢሮብ፣ ራማ፣ አኵስም፣ ዓድዋ፣ በደቡብ አቅጣጫም አላማጣ፣ ራያ አላማጣ፣ ኮረም፣ እንዲሁም ወጅራት አካባቢ ተዘርፏል ማለት ይቻላል፡፡” ያሉት አቶ ገብረ እግዚአብሔር “በመጨረሻው ጦርነት ወቅትም፣ በዓዲ ሃገራይ እና በሸራሮ፣ ከ13ሺሕ ኩንታል በላይ እህል በኤርትራ ሠራዊት ተዘርፏል፡፡” ብለዋል።
አቶ ገብረ እግዚአብሔር አያይዘው “የርዳታ እህልን ከዓላማው ውጭ ለገበያ ማዋልንና የምዝበራ ችግሮችን መፍታት፣ ለጥያቄ የማይቀርብ ጉዳይ ነው፡፡ ኾኖም፣ የትግራይ ክልል መንግሥት ያስተዳድራቸው በነበሩ የርዳታ እህል መጋዝኖች ላይ፣ አይደለም የተወረረ እና የተዘረፈ፣ በሩ እንኳን የተሰበረ መጋዘን የለም::” ብለዋል።
ኤርትራ፣ ለውንጀላው ቀጥተኛ መልስ ባትሰጥም፣ ከአሁን በፊት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት ፈጽማቸዋለች በሚል የሚቀርቡባትን ክሦች ስታስተባብል ቆይታለች::
በትግራይ ክልል፣ የርዳታ ምግብ ሊደርሳቸው የሚገቡ ሰዎችን የመለየት እና የማከፋፈል ሥራ፣ ፍትሐዊነት ይጎድለዋል፡፡ ይህንም ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ ነው፤ ሲሉ ዲሬክተሩ ገልጸዋል::
የነፍስ አድን የርዳታ ምግብ፣ ለምግብ ፈላጊዎች ብቻ የሚሰጥ እንጂ ለገበያ መዋል እንደማይገባው የገለጹት ዲሬክተሩ፣ በክልሉ በገበያ ላይ የርዳታ እህል እየተሸጠ መኾኑን አምነው፣ “ለገበያ የዋሉ የርዳታ ምግብ ቁጥጥር ጀምረናል፤ ለማስቆም እየሠራን ነው፤” ብለዋል::
ለሰብአዊ ርዳታ የሚለገሱ ምግቦች፣ በሱቆች እና በፋብሪካዎች በብዛት በመኾኑ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩበት ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ የርዳታ እህል፣ ከሌሎች ክልሎች ይልቅ በትግራይ ክልል ዋጋው ስለሚጨምር፣ ከሌሎች ክልሎችም ወደ ትግራይ ገብቶ ይሸጣል፤ ያሉት ዲሬክተሩ፣ በዚኽም የቁጥጥር ሥራ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡
ይህም ሁሉ ኾኖ፣ በትግራይ ክልል የተቋረጠው የምግብ ርዳታ ሥርጭት እንዲቀጥልና ችግር ውስጥ የሚገኘው ሕዝብ ድጋፍ እንዲደረግለት፣ ክልሉ ከርዳታ ሰጪ ተቋማት ጋራ እየተወያየ መኾኑን፣ የክልሉ ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ግብረ መልስ ዳይሬክቶሬት ዲሬክተር አቶ ገብረ እግዚአብሔር አረጋዊ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ በትግራይ ክልል ጉብኝት ያደረጉት፣ በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዲሬክተር ክላውድ ጂቢዳር፣ መሸጥ የማይገባቸው የርዳታ ምግቦች፥ በመቐለ እና በሽረ እንዳሥላሴ ከተሞች፣ በገበያ ላይ መታየታቸውንና የሕፃናት አልሚ ምግቦች ሳይቀሩ፣ በብዛት ለሽያጭ እየዋሉ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ፣ ተጨማሪ ምርመራ እንዲሚካሔድም ጠቁመዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፣ ለርዳታ ፈላጊዎች የሚለገሰውን ምግብ በመሸጥ ጽዩፍ ተግባር ላይ የተሠማሩ ግለሰቦችን ለማረም፣ ርምጃ እንደሚወሰድ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡