በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የስርቆት ተጠርጣሪዎችን መብት ጥሰዋል የተባሉ የቀበሌ ሓላፊዎች ተያዙ


የስርቆት ተጠርጣሪዎችን መብት ጥሰዋል የተባሉ የቀበሌ ሓላፊዎች ተያዙ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:52 0:00

በቦረና ዞን ያቤሎ ወረዳ፣ በርዳታ እህል ስርቆት በተጠረጠሩ አራት ወጣቶች ላይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉ፣ ስምንት የቀበሌ አስተዳደር ሓላፊዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የያቤሎ ወረዳ ወረዳ አስታወቀ።

በስርቆት ተጠርጣሪ ወጣቶቹ ላይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጽመዋል በሚል የክሥ አቤቱታ የቀረበባቸው፣ የሄርወዩ ቀበሌ ሊቀ መንበር እና ሌሎች ሰባት ሰዎች በሕግ ጥላ ሥር ውለው፣ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መኾኑን፣ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጎቡ ጨና ተናግረዋል። የያቤሎ ወረዳ ፖሊስ ሓላፊም፣ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው የክሥ መዝገብ መከፈቱን ተናግረዋል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጎቡ ጨና፣ ከትላንት በስቲያ እሑድ፣ ሚያዝያ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በርዳታ እህል ስርቆት ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ሥር በዋሉ ወጣቶች ላይ፣ በቀበሌ ሓላፊዎቹ ተፈጸመ ስለተባለው ቅጣት ሲያስረዱ፤ “በአጭሩ የተፈጸመው ነገር፣ በያቤሎ ወረዳ ሄርወዩ ቀበሌ፣ በአንድ የእህል መጋዘን ውስጥ የነበረ 12 ኩንታል የርዳታ እህል፣ ተሰርቆ ይወጣና ለአንድ ነጋዴ ይሸጣል። በበነጋው የቀበሌው አስተዳደር፣ ተሰርቆ የተሸጠውን የርዳታ እህል፣ በነጋዴው ቤት ያገኘውና ነጋዴው ሲጠየቅ፣ እህሉን የሸጡልኝ ወጣቶች ናቸው፤ ሲል ይናገራል፡፡” ሲሉ ኹኔታውን ማስረዳት ይቀጥላሉ።

“በነጋዴው የተጠቆሙት ወጣቶች ተይዘው ሲጠየቁ፣ ድርጊቱን ስለ መፈጸማቸው ይክዳሉ፡፡ ሚያዝያ 18 ቀን ወጣቶቹ በድጋሚ ቃል እንዲሰጡ ተደርገው ቢጠየቁም ድርጊቱን መፈጸማቸውን ይክዳሉ፡፡ ለሁለተኛ ቀን ፖሊስ ጣቢያ ቢያድሩም፣ አልፈጸምንም የሚለው ቃላቸው ባለመለወጡ አሳድረው ጠዋት ላይ ለቀቋቸው።ኾኖም፣ እሑድ ጠዋት ላይ በድጋሚ ይዘው አሰሯቸው።” ብለዋል።

በመሠረቱ ወጣቶቹ፣ ቀደም ሲል ድርቅ በርትቶ በነበረበት ወቅት፣ ከአካባቢው ጤና ጣቢያ፣ የልጆች ምግብ በመስረቅ ተጠርጥረው፣ ከመካከላቸው አንደኛው ተፈርዶበት ነበር፡፡ በመኾኑም፣ ከዚኽም በፊት ተመሳሳይ ስርቆት ፈጽማችኋል፤ በሚል፣ ከቀበሌው አስተዳዳሪ ትዕዛዝ እንደወረደላቸው የተናገሩትየቀበሌ ሚሊሻዎች፣ “በቦረና ነዋሪ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው አላስፈላጊ ድርጊት ፈጸሙባቸው።” ብለዋል።

በተጠርጣሪ ወጣቶቹ ላይ የተፈጸመው የሰብአዊ መብቶች ጥሰትም፣ በማኅበራዊ መገናኛ ትስስሮች መሠራጨቱን ተከትሎ የመወያያ ርእስ ኾኗል። በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት የተጋራውን የወጣቶቹን ምስል፣ የአሜሪካ ድምፅ ማረጋገጥ ባይችልም፣ በምስሉ ላይ አንደኛው ወጣት በመሬት ላይ አንደኛው ደግሞ በዕንጨት ላይ፣ በገመድ እጃቸውን የፊጥኝ ታስረው ከጎናቸው የሕግ አስከባሪ ልብስ የለበሱ ግለሰቦች ይታያሉ። በዚኽ ዐይነቱ ኢሰብአዊ አያያዝ ላይ የተሳተፉ የሄልወዩ ቀበሌ አስተዳዳሪን ጨምሮ ሌሎችም ሓላፊዎች በቁጥጥር መዋላቸውን፣ አቶ ጎቡ ጨና ተናግረዋል።

የያቤሎ ወረዳ አዛዥ ኢንስፔክተር ማልቸ ጃርሶ፣ “የቀበሌ ሓላፊዎቹ መነሻ፣ ልጆቹ ከዚኽ በፊት በስርቆት የተጠረጠሩ መኾናቸው ይመስለኛል፡፡” ካሉ በኋላ “ይኹንና፣ ተጠርጣሪዎችም ቢኾኑ ይህን አግባብነት የሌለውን ኢሰብአዊ ድርጊት ፈጽመዋል የተባሉ ስምንት ሰዎችን በቁጥጥር አውለናል፡፡ የተጠያቂዎቹ ቁጥር ከዚኽም ሊጨምር ይችላል፡፡ ጉዳዩን እያጣራን ነው፤ የክሥ መዝገብ ተከፍቶ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቀንበታል፤ ፍርድም የሚሰጥበት ይኾናል።” ብለዋል።

የያቤሎ ወረዳ አስተዳደር፣ በተጠቀሰው ኢሰብአዊ አድራጎት የተሳተፉ፣ ቀሪ ሁለት ሰዎች መኖራቸውንና ፖሊስ እያፈላለጋቸው እንደኾነም ጠቁሟል።

XS
SM
MD
LG