በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቱርክ አውሮፕላን በተፋላሚው ኃይል መመታቱን የሱዳን ጦር አስታወቀ


የቱርክ አውሮፕላን በተፋላሚው ኃይል መመታቱን የሱዳን ጦር አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:31 0:00

የቱርክ አውሮፕላን በተፋላሚው ኃይል መመታቱን የሱዳን ጦር አስታወቀ

በሱዳን ተዋጊ ኃይሎች መካከል ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባር ላይ ባለመዋሉ፣ በዋና ከተማዋ ካርቱም እና በአጎራባቿ ኦምዱርማን ከተማ፣ ከዐርብ ጠዋት ጀምሮ ከፍተኛ ፍንዳታ እና የተኩስ ልውውጥ ሲካሔድ መዋሉን ነዋሪዎች ገል ጸዋል።

በሁለቱ ጀነራሎች ምክንያት የሚካሔደው የሥልጣን ሽኩቻ፣ በመቶዎች የሚቆጥሩ ሰዎችን ለኅልፈት ዳርጓል፡፡ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን አገሪቱን ለቅቀው ለመውጣት መረባረባቸውን ቀጥለዋል።

በሱዳን እየተዋጋ የሚገኘው ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል፣ ዜጎቹን ለማስወጣት ከካርቱም ውጪ በሚገኘው ዋዲ ሴይድ አውሮፕላን ማረፊያ ሊያርፍ የነበረ የቱርክ አውሮፕላን ላይ ተኩሶ በመምታቱ፣ የነዳጅ ማስተላለፊያው ላይ ጉዳት መድረሱን፣ የሱዳን ጦር አስታውቋል።

ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል በበኩሉ፣ የቀረበበትን ክሥ አስተባብሎ በአወጣው መግለጫ፣ የጦር ሰራዊቱ፥ “ውሸት እያሰራጨ ነው፤” ብሏል። ሠራዊታችን፣ ከእኩለ ለሊት ጀምሮ ለመተግበር በተስማማው የሰብአዊ ተኩስ ማቆም ስምምነት እንደ ጸና መኾኑን ያስታወቀው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መግለጫ፣ በኦምዱርማን ከተማ በሚገኘው ዋዲ ሴይድና ማረፊያ ሊያርፍ የነበረ አውሮፕላን ዒላማ አድርገዋል የሚለው እውነት አለመኾኑን ገልጾ አስተባብሏል። የቱርክዬ መከላከያ ሚኒስትር ደግሞ፣ ዜጎቹን ለማውጣት የሚጠቀምበት አውሮፕላን እንደተተኮሰበት አረጋግጦ፣ ምንም ዐይነት ጉዳት ግን አለመድረሱን አመልክቷል።

በሱዳን ውጊያው ቀጥሏል

ሁለቱ የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች፣ የተኩስ ማቆም ስምምነቱን፣ ከኀሙስ ማታ ጀምሮ ለ72 ሰዓታት ለማራዘም እና ሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስ ለማድረግ ተስማምተው የነበረ ቢኾንም፣ በዋና መዲናዋ ካርቱም እና ጦርነት በአመሰቃቀለው የዳርፉር ግዛት ውጊያው መቀጠሉን፣ የዐይን እማኞች እና በቀጥታ የተላለፉ የቪዲዮ ምስሎች ያሳያሉ።

ባለፈው ዓርብ በአየር ኃይሎች፣ ታንኮች እና መድፎች በታገዘው ጥቃት ካርቱምን ማመሳቸውን በመቀጠላቸው፣ መዲናዋ በጥቁር ጭስ ታፍናለች። በተደጋጋሚ የተሞከሩት የተኩስ ማቆም ስምምነቶች፣ የውጭ ሀገራት ዜጎቻቸውን በተሽከርካሪዎች፣ በአውሮፕላኖች እና በባሕር ኃይሎች በመታገዝ እንዲያስወጡና በ10ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን፣ ደኅንነታቸው የሚጠበቅበትን ሥፍራ ፍለጋ እንዲሰደዱ ዕድል ከመፍጠሩ ውጪ፣ ግጭቱን ሙሉ ሙሉ ማስቆም አልቻለም።

በሱዳን ተጠባባቂ የሰብአዊ ርዳታ አስተባባሪ የኾኑት አብዱ ዲያንግ፣ ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ከግጭቱ በፊት በሱዳን የሚፈለገው ሰብአዊ ርዳታ፣ በ15 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን ያለው ቀውስ ያስከተለውን ተጨማሪ የሰብአዊ ርዳታ ፍላጎት ለመገምገም አስቸጋሪ መኾኑን አመልክተዋል።

"የሰብአዊ ርዳታ ሠራተኞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቆስለዋል። በካርቱም፣ በዳርፉር እና በመላው ሀገሪቱ ዝርፊያ እየተካሔደ ነው፤” ያሉት ዲያንግ፣ “በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ምን እየተካሔደ እንደኾነና ምን ዐይነት ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ለማወቅ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው፤” ሲሉ ገልጸዋል።

“ዩኒቨርሲቲዎች ለመሸሸጊያነት መጠቀሚያ ኾነዋል”- የዐይን እማኞች

በዚኽ ውጊያ አጣብቂኝ ውስጥ ከገቡት መካከል፣ በሱዳን ይማሩ የነበሩ ናይጄሪያውያን ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡ ካርቱም የሚገኘው የዩኒቨርሲቲ ካምፓስ፣ ለተፋላሚው የአርኤስኤፍ ኃይል እንደ ምሽግ እያገለገለ መኾኑንና ከሀገር የመውጣቱ ሒደት እጅግ መንቀራፈፉን በመግለጽ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርቱን ይከታተል የነበረው የ24 ዓመቱ ወጣት ኡመር ዩሱፍ፣ ለሮይተርስ እንደገለጸው፣ የናይጄሪያ ዜግነት ያላቸው ተማሪዎች፣ ምግብም ኾነ ንጹሕ ውኃ ሳያገኙ ለአራት ቀናት በዚያው በትምህርት ተቋማቸው ሲጠብቁ ቆይተዋል። በቪዲዮ የተቀረጸው ምስልም፣ በከፍተኛ ኹኔታ የተጨነቁ ሰዎች፣ ከዩኒቨርሲቲው ውጪ ሻንጣቸውን ይዘው ቆመው ሲጠባበቁ ያሳያል።

ዩሱፍ፣ “ከዚኽ ሥፍራ የማስወጣቱ ሒደት፥ በደንብ ያልተደራጀና አስፈላጊውን ነገር ያልያዘ ነው። ላለፉት አራት ቀናት ተማሪዎች ታግተዋል። የምግብ፣ የንጹሕ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የለም፤ አሁን ቁጭ ባልንበት ራሱ በየቦታው ማለት ይቻላል የጥይት ድምፅ ይሰማል። እዚኽ ደኅንነታችን የተጠበቀ አይደለም፤” ሲልም ስጋቱን ገልጿል።

የሱዳን ግጭት ከተባባሰ ወዲህ፣ የውጭ ሀገራት ዲፕሎማቶቻቸውንና ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ጥረት እያደረጉ ቢኾንም፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ናይጄሪያውያን ግን፣ አሁንም ካርቱም ከሚገኘው የአፍሪካ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርስቲ የሚያስወጣቸውን ለማግኘት እየተጠባበቁ ነው።

የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሐሙዱ ቡሃሪ፣ መንግሥት ተማሪዎች የኾኑትን አብዛኞቹን ዜጎቹን ወደ ግብጽ ለማስወጣት፣ 250 አውቶቡሶችን ለመቅጠር ዐቅዶ የነበረ ቢኾንም፣ እስከ አሁን ማግኘት የቻለው 40 አውቶብሶችን ብቻ እንደኾነ አስታውቋል።

ዑመር ዬሱፍ ያሩ የተሰኘ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ፣ “ዋናው ችግር የአርኤስኤፍ ወታደሮች የዩኒቨርሲቲውን አካባቢ መክበባቸው ነው፤” ሲል ስጋቱን ገልጿል፡፡ አክሎም፣ “እኛን እንደ መከላከያ ጋሻ እየተጠቀሙብን ነው። ምክንያቱም፣ ተማሪዎችን ከከበቡ የቦምብ ጥቃት ዒላማ አይኾኑም፤” በማለት ተማሪዎቹ የጥቃት ሰለባ እንዳይኾኑ ያለባቸውን ፍርሃት አጋርቷል።

ናይጄሪያ፣ በሱዳን ከፍተኛ የተማሪዎች ቁጥር ካላቸው ሀገራት ተርታ የምትመደብ ሲኾን፣ በሱዳን የሚገኙ 5ሺሕ500 ዜጎቿን ለማስወጣት የሚያስችል ኹኔታ እንዲፈጠርላት ጠይቃለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኢትዮጵያ በሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ታግዘው፣ በኢትዮጵያ በኩል ከሱዳን መውጣት የቻሉ 49 የቻይና ዜጎች፣ ኀሙስ ጠዋት ከዐዲስ አበባ ተነሥተው ወደ አገራቸው መግባታቸውን፣ ቻይና አስታውቃለች። በተለያዩ አካላት ትብብር፣ በሁለት ዙር ከሱዳን የወጡት የቻይና ዜጎች፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻርተር አውሮፕላን ታግዘው አዲስ አበባ የደረሱት፣ ረቡዕ ዕለት ነበር።

ከሱዳን መውጣት ከቻሉት ነዋሪዎች መካከል አንዱ የኾነው ቻይናዊ ጂን ዙቴንግ ስለኹኔታው ሲገልጽ፣ “በኤምባሲያችን ሠራተኞች ጥረት፣ ትላንት ማክሰኞ ከሱዳን ተነሥተን ከሁለት ሰዓት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ገብተናል። የቀረውን ጊዜ ያሳለፍነው በመንገድ ላይ ነበር። ትላንትና ከሀገር ስንወጣ የነበረው ኹኔታ ግን ቀላል ነበር፤” ብሏል።

መውጫ አግኝተው ወደ ሱዳን ድንበር መድረስ ለቻሉ ሁሉም የውጭ ዜጎች ግን፣ ከሀገር መውጣት እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም። የውጭ ዜጎችን ከሱዳን በማስወጣት ድጋፍ እየሰጠ የሚገኘው “ጊፍት ኦፍ ጊቨርስ” የተሰኘ የደቡብ አፍሪካ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት መሥራች ኢምቲያዝ ሱሊማን እንዳስታወቁት፣ በአንደኛው አውቶቡሱ ከጫናቸው ሰዎች የተወሰኑቱ፣ ፓስፖርታቸውን ሱዳን ጥለው በመምጣታቸው፣ ሌሎች ደግሞ በቂ የመጓጓዣ ሰነድ የሌላቸው በመኾኑ ወደ ግብጽ እንዳይገቡ ተከልክለዋል።

“ትልቁ ችግር፣ አብዛኞቹ ሰዎች ፓስፖርት የላቸውም። ፓስፖርት ከሌለ ደግሞ ድንበር ላይ ትልቅ እክል ይኾናል። ስለዚኽ ከብዙ ሀገራት የመጡ በርካታ ሰላማውያን ሰዎች በድንበር ላይ አሉ፤” ያሉት ሱሊማን፣ “ሁሉም የዲፕሎማሲ ሥራዎች ተዘግተዋል። ምንም ዐይነት የቆንስላ ድጋፍ የለም። ስለዚህ መውጣት አይችሉም። የባንክ አገልግሎትም ስለሌለ ገንዘብ የለም፤ ምግብ የለም፤ ሥራ የለም። ሰዎቹ መውጣት ይፈልጋሉ፤” ሲሉ፣ መንግሥታት ዜጎቻቸውን ለማስወጣት መደረግ ያለበትን ኹሉ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሱዳን ግጭት ወደ ውክልና ጦርነት እንዳያመራ ስጋት አለ

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሱዳን ውስጥ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሲካሔድ የሰነበተው ውጊያ፣ ሀገሪቱን ለከባድ ድህነት እና ብጥብጥ እያጋለጣት ነው፤ ሲሉ፣ አንድ ከፍተኛ የአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣን አሳስበዋል።

የአህጉራዊው ኅብረት የፖለቲካ የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነሩ ባንኮሌ አዴዎዬ፣ ረቡዕ ዕለት ለጋዜጠኞች በአደረጉት ገለጻ፣ የአፍሪካ ኅብረት በሱዳን ውጊያ አንዳችም የውጭ አካል ጣልቃ ገብነት እንዲኖር አይፈቅድም፤ ማለታቸው ተመልክቷል።

በካርቱም እና በሌሎችም ከተሞች፣ በኤሌክትሪክ፣ በውኃ እና በሌሎችም ወሳኝ ብሔራዊ የመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ፣ መጠነ ሰፊ ውድመት እየደረሰ መኾኑን ባለሥልጣኑ በጉልሕ አንሥተዋል፡፡ አያይዘውም፣ “የሱዳን ኢኮኖሚ ከግጭቱም በፊት አስከፊ ደረጃ ላይ ነበር። አሁን ደግሞ መላው ሱዳን፣ በቀውስ ላይ ቀውስ ተደራርቦታል። ይህ ድርብርብ አደጋ ነው፤” በማለት ውጊያው ያቺን ሀገር ሊቀለበስ የማይችል ጉዳት ላይ እንደሚጥላት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ተፋላሚዎቹ ኃይሎች እንዲነጋገሩ ለመሸምገል የተቻለውን ሁሉ እያደረገ መኾኑን የተናገሩት አዴዎዬ፣ የአህጉራዊው ኅብረት ኹኔታውን እየተከታተለ መኾኑን አመልክተዋል። አፍሪካውያን የራሳቸውን ጉዳይ ራሳቸው መምራት እንደሚችሉ የአፍሪካ ኅብረት እንደሚያምን የገለጹት ባለሥልጣኑ፣ የውጭ ተዋናዮችን ጣልቃ ገብነት እንደሚያወግዝ አስምረው፣ ግጭቱ ወደ ውክልና ጦርነት እንዳያመራ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከኅብረቱ ጋራ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።

XS
SM
MD
LG