በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በምዕራብ ሱዳን - ዳርፉር ለቀናት በዘለቀ ግጭት 14 ሰዎች ሞቱ


በዳርፉር ያሉ ሕጻናት በግጭት ወቅት ተሰባስበው ይታያሉ (ፎቶ ፋይል AFP የካቲት. 2, 2021)
በዳርፉር ያሉ ሕጻናት በግጭት ወቅት ተሰባስበው ይታያሉ (ፎቶ ፋይል AFP የካቲት. 2, 2021)

በምዕራብ ሱዳን ለረጅም ጊዜ በቀውስ ስትታመስ በቆየችው ዳርፉር ክልል፣ ባለፉት ሦስት ቀናት በነገዶች መካከል በተፈጠረ ደም አፋሳሽ ግጭት፣ በጥቂቱ 14 ሰዎች መገደላቸው፣ የአገር ውስጥ የመብት ተሟጋቾች ተናገሩ፡፡

ባለፈው እሑድ፣ በምዕራብ ዳርፉር ክፍለ ግዛት በምትገኘው የፉር ባራንጋ ከተማ፣ ጠመንጃ ይዞ በሞተር ብስክሌት ሲጋልብ የነበረ አንድ አረብ ታጣቂ፣ ተኩስ በመክፈት አንድ ነጋዴ መግደሉን፣ የመብት ተሟጋቾቹ ገልጸዋል፡፡

ይኸው ግድያ በቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ፣ በአረብ እና በአፍሪካውያን ነገዶች መካከል በተፈጸሙ መጠቃቃቶች ዝርፊያ መፈጸሙን፣ በዳርፉር መጠለያ ካምፕ፣ ስደተኞችን የሚረዳው አንድ የአገር ውስጥ ድርጅት ቃል አቀባይ አስታውቋል፡፡

ግጭቱ እስከ ትላንት ማክሰኞ ድረስ መቀጠሉንና የሟቾችም ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የአሶስየትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ባለፈው ማክሰኞ፣ የምዕራብ ዳርፉር መንግሥት፣ በአወጣው ለኹለት ሳምንት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ፣ የምሽት እንቅስቃሴን የሚገደብ የሰዓት እላፊ መጣሉ ተዘግቧል፡፡

XS
SM
MD
LG