በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጣልያን በፍልሰተኞች ጉዳይ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አወጣች


በጀልባ ወደ ጣልያን የሚያመሩ ፍልሰተኞች (ፎቶ AFP መጋቢት 3፣ 2023)
በጀልባ ወደ ጣልያን የሚያመሩ ፍልሰተኞች (ፎቶ AFP መጋቢት 3፣ 2023)

የጣልያን ቀኝ አክራሪ መንግሥት፣ በአገሪቱ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ በኩል እየጨመረ የመጣውን የፍልሰተኞች ቁጥር ለመቆጣጠር፣ ትላንት ማክሰኞ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማውጣቱን፣ የጣልያን ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡

የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እና ካቢኔያቸው፣ ለስድስት ወራት የሚቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን አጽድቀዋል።

በላምቤዱሳ የሚገኘው የፍልሰተኞች መጠለያ፣ ቀደም ሲል ወደ ጣልያን በዝርወት ለሚመጡ ከለላ ጠያቂዎች፣ የመጀመሪያው መዳረሻ ኾኖ ቆይቷል። ኾኖም መጠለያው፣ በቁጥር እየበዙ በመጡ ፍልሰተኞች በመጥለቅለቁ ለማስተናገድ አስቸጋሪ ስፍራ ኾኗል፡፡

ትላንት ማክሰኞ ብቻ፣ በመጠለያ ጣቢያው ከነበሩ 1ሺሕ 600 ፍልሰተኞች መሀከል እንኳ፣ የአየር ኹኔታው እንደተሻሻለ፣ 400 የሚኾኑቱ ምሽቱን ከአካባቢው እየለቀቁ በጀልባ እንደሚሔዱ ተስፋ አድርገዋል፡፡

የመጠለያ ማዕከሉ ዳይሬክተር ሎሪና ቶርቶሪቺ ስካይ፣ ሕፃናት እና አዳጊዎችን ያስከተሉ ብዙ እናቶች፣ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ እንደሚገኙ፣ ቲጂ24 ለተባለው የጣልያን ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

የአኹኑ የአውሮፓውያን ዓመት ከጀመረበት አንሥቶ፣ ያለምንም ድጋፍ ከጣልያን ድንበር የደረሱ 31ሺሕ ፍልሰተኞች፣ በጣልያን ወታደራዊ ጀልባ ወይም የበጎ አድራጊ መርከቦች መጓጓዛቸውን፣ ከጣልያን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

እስከ አኹን፣ ትልቅ ቁጥር ያላቸው ፍልሰተኞች ወደ ጣልያን የሚመጡት፥ ከአይቮሪ ኮስት፣ ጊኒ፣ ፓኪስታን፣ ግብጽ፣ ቱኒዝያ እና ባንግላዴሽ እንደኾነ፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ጠቁሟል፡፡

XS
SM
MD
LG