የቱኒዚያ የባህር ድንበር ጠባቂዎች ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሞከሩ 14 ሺህ ፍልሰተኞችን መያዛቸውን አስታወቁ። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ግዜ ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ በአምስት ዕጥፍ ያደገ ነው ተብሏል፡፤
አብዛኞቹ ፍልሰተኞች ከሳሃራ ግርጌ ካሉ አገራት ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሞከሩ ናቸው ሲል መግለጫው አስታውቋል።
ባለፈው ወር የቱኒዚያው ፕሬዝደንት ካይስ ሳይድ ከአህጉሪቱ የሚመጡ ስድተኞችን ያሚያጥላላ ንግግር ከተናገሩ በኋላ፣ ፍልሰተኞቹ ከተከራዩበት ቤት እንዲወጡና ጥቃት እንዲደርስባቸው አድርጓል። በደርዘን የሚቆጠሩትም ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሲሞክሩ ባህር ውስጥ ሰምጠዋል።
የጣልያን መንግስት በበኩሉ ባለፉት ሶስት ወራት 14 ሺህ የሚሆኑ ፍልሰተኞች ወደ አገሪቱ መግባታቸውን አስታውቋል። ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ግዜ ጣልያን የገቡት ፍልሰተኞች 5ሺህ 300 እንደነበር መንግስት ጨምሮ ገልጿል።