በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጋራ ግብረ ኃይሉ ታሳሪዎች የችሎት ውሎ እና የተጠርጣሪ ቤተሰቦች አስተያየት


የጋራ ግብረ ኃይሉ ታሳሪዎች የችሎት ውሎ እና የተጠርጣሪ ቤተሰቦች አስተያየት
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:12 0:00

የጋራ ግብረ ኃይሉ ታሳሪዎች የችሎት ውሎ እና የተጠርጣሪ ቤተሰቦች አስተያየት

“በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ላይ ጥቃት በመፈጸም፣ ሀገራዊ ሁከት እና ብጥብጥ ለመቀስቀስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖችን በቁጥጥር ሥር አውያለኹ፤” ሲል፣ የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ትላንት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል፣ በግብረ ኃይሉ መግለጫ ላይ የተጠቀሱ አምስት ግለሰቦች እና በመግለጫው ስማቸው ያልተጠቀሰው የባልደራስ ምክትል ፕሬዝደንት፣ በአንድ መዝገብ ሥር በፍርድ ቤት ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ናቸው፡፡

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የመጀመሪያ ደረጃ ችሎት፣ ከመካከላቸው ለአንድ ግለሰብ ዋስትና ሲፈቀድላቸው፣ በሌሎቹ ላይ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ የሰጠ ሲኾን፣ ይህን በመቃወም ይግባኝ መጠየቃቸውን፣ ከጠበቆቻቸው አንዱ ሰሎሞን ገዛኸኝ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ የሚገኙት፣ የረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው ባለቤት በሰጡን አስተያየት፣ “እየለመነ የተፈናቀሉ ወገኖችን ከመርዳት ውጭ ሌላ ተግባር የለውም፤ ፈጣሪ ፍርዱን ይስጥ፤” ሲሉ፣ ባለቤታቸው ርዳታ በማሰባሰብ ሥራ ላይ ከመሠማራታቸው ውጭ፣ በወንጀል ሊያስጠረጥራቸው የሚችል ነገር አለ ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ በትላንት መግለጫው፣ መቀመጫቸውን፣ በአማራ እና በሌሎች ክልሎች ያደረጉ ምሁራንን፣ የሚዲያ ባለቤቶችንና አክቲቪስቶችን ያካተተ ኅቡእ መዋቅር፣ ሀገራዊ ሁከት እና ብጥብጥ ለማሥነሳት በምስጢር ሲንቀሳቀስ ነበር፤ ሲል አስታውቋል፡፡

“በኅቡእ አደረጃጀቱ ሲሳተፉና ሲያስተባብሩ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤” ያላቸውን ግለሰቦችንም በዝርዝር ጠቅሷል፡፡ ግብረ ኃይሉ ከዘረዘራቸው ተጠርጣሪዎች መሀከል አምስቱ፣ ከትላንት በስቲያ ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ፣ ለአሜሪካ ድምፅ የገለጹት፣ ከጠበቆቻቸው አንዱ የኾኑት የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ ሰሎሞን ገዛኸኝ፣ በዝርዝሩ ውስጥ ስማቸው ያልተጠቀሰው የባልደራስ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አምኃ ዳኘው፣ ከአምስቱ ተጠርጣሪዎች ጋራ በአንድ መዝገብ ክሥ እንደተከፈተባቸው ተናግረዋል፡፡

በመግለጫው ከተጠቀሱት ግለሰቦች መካከል አምስቱ፣ በረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው መዝገብ ሥር ክሥ የተከፈተባቸው መኾናቸውን፣ ከጠበቆቻቸው አንዱ ሰሎሞን ገዛኸኝ ገልጸዋል፡፡ ከስድስቱ ግለሰቦች በአምስቱ ላይ፣ ፍርድ ቤት የሰጠውን የ14 ቀን ቀጠሮ በመቃወም ይግባኝ ማቅረባቸውንም ጠበቃው ገልጸዋል፡፡

ስለ ግለሰቦቹም ማብራሪያ የሰጡን ጠበቃው፣ ከአምስቱ መካከል፣ በብዙኃን መገናኛ የተሰራጨው እና ግብረ ኃይሉ የጠቀሰው የአንደኛው ተጠርጣሪ ስም እና ፎቶ የተለያየ ስለ መኾኑ፤ እንዲሁም፣ የባልደራስ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አምኃ ዳኘው፣ በክሥ መዝገቡ ቢካተቱም፣ በግብረ ኃይሉ መግለጫ ላይ ግን አለመጠቀሳቸውን ተናግረዋል፡፡

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ መምህር ኄኖክ ዐዲሴ፣ በፍርድ ቤት ጉዳዩን በመከታተል ላይ የሚገኝ ሌላው ተጠርጣሪ ሲኾን፣ የቤተሰቡ አባል እንደኾነ የነገረኝ አቶ ሙሉጌታ ዓለሙ፣ ዛሬ ወደ እስር ቤት አምርቶ ኄኖክን እንደጠየቀው ገልጿል፡፡ “በቀረበበት ክሥ እርሱም በጣም ነው ‘ሳርፕራይዝድ’ የኾነው (የተገረመው)፤ እኛም ግራ ተጋብተናል፤” በማለት አቶ ሙሉጌታ አስተያየቱን አጋርቶናል፡፡

በዚኽ ዙሪያ የተሰናዳውን ሙሉ ዘገባ ለማድመጥ የተያያዘውን ፋይል ይጫኑ።

XS
SM
MD
LG