በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ያለመኖሪያ ፈቃድ በሱዳን የሚኖሩት ደቡብ ሱዳናውያን


ያለመኖሪያ ፈቃድ በሱዳን የሚኖሩት ደቡብ ሱዳናውያን
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:24 0:00

ያለመኖሪያ ፈቃድ በሱዳን የሚኖሩት ደቡብ ሱዳናውያን

ደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን ተነጥላ ዐዲስ አገር ከኾነች ዐሥር ዓመታት ቢያልፉም፣ ቁጥራቸው ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ደቡብ ሱዳናውያን፣ የኹለቱንም ሀገራት ዜግነት ሳያገኙ፣ ዛሬም በሱዳን በመኖር ላይ መኾናቸውን፣ የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት አመለከተ።

ሄንሪ ዊልከንስ፣ በሱዳን - ካርቱም አግኝቶ ያነጋገራቸው፣ የዜግነት ማረጋገጫ ሰነድ ወይም ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያላገኙ ብዙዎች፣ የሥራ ዕድልም ኾነ ትምህርት እና ሕክምና ለማግኘት ብርቱ ፈተና ይገጥማቸዋል።

ካርቱም ውስጥ፣ ባጃጅ በማሽከርከር የሚተዳደርና በመንግሥት ሊደርስ የሚችልን ቅጣት በመፍራት የአባቱን ስም ከመግለጥ የተቆጠበ፣ በሽር የተባለ የ19 ዓመት ወጣት ስደተኛ፣ ኮሌጅ ገብቶ ትምህርቱን መከታተል ቢፈልግም፣ የሱዳን ዜግነት ስለሌለው ማሳካት አለመቻሉን ይናገራል።

“የኹለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እስከ ሦስተኛ ዓመት ድረስ ተምሬያለኹ። ኾኖም፣ ኮሌጅ ለመግባት ሕጋዊ የትምህርት ማስረጃ የለኝም። ስለዚኽ፣ ተፈላጊ የትምህርት ማስረጃዎቼን እስካገኝ ድረስ ሥራ ለማፈላለግ ሞከርኹ። ኾኖም፣ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ብቻ ላለው ሰው፣ ምንም ዓይነት የሥራ ዕድል የለም። ይህን ኹኔታ ማስተካከል ወይም መለወጥ አልችልም።”

በሽር፣ ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ከአገኘችበት እ.አ.አ ከ2011 ዓ.ም. አንሥቶ፣ በሱዳን፣ የዜግነትም ኾነ የመታወቂያ ደብተር ማግኘት ካልቻሉ አያሌ የደቡብ ሱዳን ተወላጆች አንዱ ነው። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን(UNHCR) እንደሚለው፣ ቁጥራቸው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚደርሱ የደቡብ ሱዳን ተወላጆች፣ በዚያች አገር በተመሳሳይ ኹኔታ ውስጥ ይኖራሉ።

ከ2011 ክፍፍል በኋላም፣ ሰዎች የዜግነት መብት እንዲያገኙ ለማድረግ የተቀረጸው ሕግ፣ ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ እንዳይውል በመደረጉ፣ የሱዳን መንግሥት፣ በደቡብ ሱዳን ተወላጅነታቸው ከሚያውቃቸው በስተቀር፣ ከደቡብ ሱዳን ጋራ ቁርኝት ለሌላቸው ብዙዎች ብርቱ ዕንቅፋት እንደጋረጠ ነው።

ኢብራሂም አልማዝ ዴንግ፣ ከዛሬዋ ደቡብ ሱዳን ወደ ካርቱም ገና በልጅነ ነበር የመጡት። “እንደምታየው ታምሜአለኹ። በሕክምና በመረዳት ላይ ነኝ። ኾኖም፣ ከውጭው ዓለም ተቆራርጫለኹ። ሐኪሞቼ ወደ ውጭ አገር ሔጄ እንድታከም መክረውኝ ነበር። ነገር ግን እንዴት አድርጌ? ወንድሜ ለጉዞው የሚያስፈልጉትን ማስረጃዎችን አስገብቶ ነበር። የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ እና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርም ማረጋገጫ ሰጥተው ነበር። ይኹንና ፕሬዝዳንቱ፣ አሁንም ድረስ አልተቀበሉትም። ይኸው አሁን ስምንት ወራት አልፎታል።”

ማህዲ ማዳኒ፣ ሕጋዊ የመኖሪያ ሰነድ የሌላቸውን ወገኖች ለመርዳት የተቋቋመው፣ የመብቶች ተሟጋቹ፣ የደቡባዊ ሱዳን የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ድርጅት ፕሬዝዳንት ናቸው። "ዜግነት ለማግኘት ማረጋገጫ ያስፈልጋል፤ የሚል ሕግ በመኖሩ፣ አሁን ያለው መንግሥት፣ እስከ አሁን ያደረገው ነገር የለም። ይህ፣ ከደቡብ ሱዳን ለሚመለሱ ሰዎች በጣም ኹኔታውን አዳጋች አድርጎታል፤” ይላሉ የድርጅቱ ፕሬዝዳንት፡፡

የማንነት ማረጋገጫ ሰነድ የሌለው ሰው፣ በሱዳን ውስጥ ለተወሰኑ ዓመታት መኖሩን የሚመሰክርለት፣ የሱዳን ዜግነት ያለው ሰው ስም፣ ለባለሥልጣናቱ መስጠት እስካልቻለ ድረስ፣ የመታወቂያ ደብተር ማግኘት አይችልም። ቁጥራቸው 6,000 ለሚደርሱ ሰዎች ብቻ፣ ዜግነት እንዲያገኙ መርዳት መቻሉን፣ ማዳኒ አክለውም አስረድተዋል።

የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት እንደሚለው፣ ኹኔታው፣ ከሕግ አንጻር ውስብስብ እና ሰዎች ”ከየትኛው ሀገር ጋራ የተቆራኘ መንፈስ እና ስሜት አላቸው“ ከሚለው እሳቤ ጋራ የተሳሰረ እንደመኾኑ፣ “እንዲህ ነው ብሎ” ለመደምደም ያስቸግራል።

በርካቶች ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለጹት፣ ደቡብ ሱዳናውያኑ፣ ሱዳን ውስጥ መኖር የሚያስችል ሕጋዊ የስደተኛ መታወቂያ የማግኘት ዕድል ቢሰጣቸውም፣ ለመገለል የሚዳርግና የሥራ ዕድልም የሚነፍግ በመኾኑ፣ በዕድሉ ለመጠቀም ፈቃደኛ ሳይኾኑ ቀርተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን የሱዳን ቢሮ ተወካይ አሌክስ ቢስቾፕ እንደሚሉት፣ መፍትሔው ማተኮር ያለበት፣ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ሰዎች ‘እንዴት ይኹኑ’ በሚለው ላይ ነው።

"ሱዳን፣ የዚያች አገር ዜጋ መኾንና ያለመኾናቸው ገና ከሚረጋገጥላቸው ቁጥራቸው የበዙ ሰዎች ተጠቃሚ ትኾን ዘንድ፣ከኅብረተሰቡ ጋራ ሰፊ መስተጋብር እንዲኖራቸው የተደረጉ ነው።"

ይህን ሰፊ ኅብረተሰባዊ መስተጋብር ማስቻያ መንገዶች አንዱ፣በምዕራብ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ኅብረት(ECOWAS) እንዳለው ኹሉ፣ በምሥራቅ አፍሪካም፣ ነጻ እንቅስቃሴ የሚፈቅድ የሥራ እና የሠራተኞች ስምምነት ሊኾን ይችላል፤ ብለዋል። ይኹን እንጂ፣ ዓመታትን ሊወስድ በመቻሉ፣ እንደ በሽር ኮሌጅ ገብተው የመማር ፍላጎታቸውን ማሳካት ለሚያልሙቱ፣ በእጅጉ የዘገየ አማራጭ ሊኾን ይችላል።

/ዘገባው የሄንሪ ዊልከንስ ነው አሉላ ከበደ ወደ አማርኛ መልሶታል/

XS
SM
MD
LG