በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዕድሜ የገፉ አሜሪካውያን በፍሎሪዳ የጡረተኞች ሰፈር ተዝናንተው ይኖራሉ


በዕድሜ የገፉ አሜሪካውያን በፍሎሪዳ የጡረተኞች ሰፈር ተዝናንተው ይኖራሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:43 0:00

“እዚያ ኹሉም ነገር ጡረተኞች ማድረግ በሚሹት ላይ ያተኮረ ነው”

በማዕከላዊ ፍሎሪዳ፣ “ዘ ቪሌጅስ” በተሰኘው የጡረተኞች ሰፈር የሚኖሩ አሜሪካውያን፣ የረጅም ዕድሜ ባዕለጸጋ ወደሚኖረው የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ የመግባት ፍላጎት የላቸውም፡፡

“መደነስ እወዳለኹ፤” የሚሉት የኒው ጀርሲው ተወላጅ ማይክል ሮሽ፣ “በየምሽቱ የሙዚቃ ዝግጅት አለ፡፡ ያ ነው ወደዚኽ የሳበኝ:: በዚያ ላይ የተፈለገውን ያህል ማዳመጥ ይቻላል፤” በማለት ያስረዳሉ።

በፍሎሪዳ 22 ሚሊዮን ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ከአምስት ሰዎች አንዱ፣ ዕድሜው ከ65 ዓመት በላይ ነው፡፡ ሞቃታማው አየር፣ የቅናሽ ዋጋው እንዲሁም፣ ጡረተኞች በሚኖሩባቸው አንዳንድ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶች፣ ጡረተኞቹን ወደ ፍሎሪዳ ይስቧቸዋል፡፡

ፒትስበርግ ውስጥ የኮንስትራክሽን ሠራተኛ የነበሩት ጡረተኛው ሬይ ሄንሪ፣ ፍሎሪዳን ለመጎብኘት ከመጡ በኋላ አልተመለሱም።

“ጠዋት ተነሥቶ ወደ እዚህ መምጣት፣ ጓደኞችን ማግኘት፣ ትንሽ መደነስ፣ አንድ ኹለት መጠጣት፣ ጥሩ ምግብ ወደሚገኝባቸው ሔዶ መብላት እና በሚቀጥለው ቀን ይህንኑ መድገም፤” እንደሚያዝናናቸው ይናገራሉ።

“እዚህ ያለው ኹሉም ነገር ጡረተኞች ማድረግ በሚፈልጉት ላይ ያተኮረ ነው፤” የሚሉት የቴክሳሷ ደኒስ ሞሊና በበኩላቸው፣ ምን ዓይነት ስሜት እንዳላቸው፣ ምን እንደሚያስደስታቸው፣ ምን ዓይነት ሙዚቃ እንደሚወዱ ታስቦበት እንደሚደረግ ይናገራሉ።

“ዘ ቪሌጅስ” በተሰኘው መንደር፣ 80 ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ በዓለም ካሉ ታላላቅ የጡረታ መንደሮች አንዱ ነው፡፡ ጎልፍ፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ክለቦች እና ሙዚቃ የሚቀርቡባቸው አደባባዮች ይገኛሉ፡፡ ሎረን ሪቺ፣ ከጡረታ በፊት ኦርላንዶ ሰንቲነል በተሰኘው ጋዜጣ ላይ ዓምደኛ ነበሩ።

“’ቦታውን፣ በዕድሜ የገፉ ሰዎች፣ ‘ዲዝኒ’ በማለት ይጠሩታል፤ በትክክልም እንደዚያ ነው፡፡ እንዲያ ባለው ሥፍራ መኖር የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፡፡ ሌሎቹም ለቤተሰብ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ እነርሱ የልጅ ልጃቸውን ከሚያዩበት አካባቢ ሳይርቁ ይኖራሉ፡፡”

በዕድሜ ለገፉ እና ጸጥታ በሰፈነበት ለመኖር ለሚሹ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ሌሎች አማራጮች አሏቸው፡፡ ሻረን ዉተን፣ በፍሎሪዳ ቤት አሻሻጭ ናቸው፡፡ “ለእያንዳንዱ እንደ ምርጫው የሚመቹ በርካታ የመኖሪያ መንደሮች አሉ፡፡ አንዱ መንደር ለአንዱ ላይመቸው ይችላል፤ ሌላው ሰው ግን ሊወደው ይችላል፡፡”

ባርብራ ዊስ፣ ሃውቶርን በተባለው መንደር የሚመቻቸውን ቦታ አግኝተዋል፡፡ በተስማሚ የአየሩ ጠባይዕ፣ ከሰዎች ጋራ ስላለው መልካም ግንኙነት እንዲሁም ራሳቸው ሕይወትን በዐዲስ መንገድ እንደገና ለመኖር በመወሰናቸው ቦታውን መርጠውታል፡፡ “ስፖርት፣ የሥነ ጥበብ ሥራዎች፣ የካርታ ጨዋታዎች የመሰሉ ከመቶ በላይ የጊዜ ማሳለፊያዎች አሉት፡፡ በተለምዶ በወጣቶች ብቻ የሚዘወተሩ ነገር ግን ለጡረተኞች የሚኾኑ ናቸው፡፡”

በዚኽ በተከለለ ግቢ የሰፈነው የደኅንነት ስሜትም፣ ተመራጭ የሚያደርገው ነገር ነው፡፡ ባርብራ በዚህ ላይ የሚያክሉት አለ፤“ቤታችን ውስጥ መጥሪያ አለ፡፡ ታዲያ ድንገተኛ ችግር ከገጠመን መጥሪያውን መጫን ነው፡፡ ሰዎች ወዲያው ይመጣሉ፡፡”

አሁን ባርብራ እና የ90 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ ባለቤታቸው፣ 30 ዓመታት ካሳለፉበት የጡረታ መንደር ወጥተው፣ ርጋታ ወደአለበትና የልጅ ልጆቻቸውን ወደሚያገኙበት ሜይን ክፍለ ግዛት ሊመለሱ ተዘጋጅተዋል፡፡ “እውነቱን እንነጋገር፤ ለዘላለም ጤነኛ ኾኖ መኖር አይቻልም፡፡ ትንሽ ችግር ሲያጋጥም፣ ቤተ ሰዎችሽ በአቅራቢያው ይገኛሉ፡፡”

ባርብራ ሥፍራውን በመልቀቃቸው ኀዘን አይሰማቸውም፡፡ በተቃራኒው በ87 ዓመታቸው፣ ዐዲስ የሕይወት ምዕራፍ ለመጀምር ዕድሉን ስላገኙ ደስተኛ ናቸው።

/የቪኦኤዋ ዶራ መክዋር ከኦርላንዶ ያጠናቀረችው ዘገባ ነው/

XS
SM
MD
LG